በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በስፋት ወደ ገበያው ለማስገባት ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በፍጥነት፣ በጥራትና በስፋት ወደ ገበያው ለማስገባት ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።   

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።  


   

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ ርእዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

አውደ ርዕዩ ስታርት አፖች ያላቸው ምርት፣ አገልግሎትና ፈጠራዎች ተቋማት፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ተማሪዎች እንዲጎበኙ ማድረግ ያለመ ነው።  

በባለኃብቶችና በስታርት አፖች መካከል ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ ሌላው የአውደ ርዕዩ ዓላማ ሲሆን ስታርት አፖች ያላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል፤ ክፍተት የሚታይባቸውን ቦታ ለይቶ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትም እንዲሁ። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በፍጥነት፣ በጥራትና በስፋት ወደ ገበያው እንዲገቡ ሥነ ምህዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው።  

በትምህርት ፖለሲ ደረጃ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርቶች ትኩረት መሰጠቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ዕዳን ወደ ምንዳ ለመለወጥ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በዲጂታል ዘርፉ ኦንላይን አገልግሎቶች በስፋት ተግባራዊ መደረጉ በመስኩ ወደ ገበያው የሚገቡ ስታርት አፖች ቁጥር ከፍ የማድረግ አወንታዊ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት አቅጣጫ ስታርት አፖች ያሉ መልካም ዕድሎችን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ የመደገፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ለዚህም የፖለሲና ማበረታቻ ድጋፎች አሰራር በመዘርጋቱ የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የድጋፍ ማዕቀፎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ለመደገፍና ለማበረታታት የተዘረጋው አሰራር የውጭ ስታርት አፖችን የሚጋብዝ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውድ ርዕይ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶች፣ ፈጠራዎችና ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን ጠቅሰው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣም ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል። 

ለዚህም ከመስሪያ ቦታ አቅርቦት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን የሚያገኙበት ሁኔታዎች ማመቻቸት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ደግፎ ወደ ገበያ እንዲገቡ ማድረግ በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ሌሎችም መስኮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድም የስታርት አፖች አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።    

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርት አፖች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም