የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ጋር ተፈራርመዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ የደም ስር ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እና ዘመኑን የዋጀ በማድረግ ውጤታማነቱን እንደሚያሳድግ አመላክተዋል።

የተደረገው ስምምነት የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም ቴክኖሎጂን በማበልጸግ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አሰራርን ማዘመን በራሱ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ኢንስቲቲዩቱ አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝ በማድረግ ምርታማነት እንዲጨምር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶች የአገልግሎት ዘርፉ እንዲዘምን እና እንዲሳለጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል።

ኢንስቲቲዩቱ በስምምነቱ በመታገዝ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያዘምኑና ችግሮችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ስምምነቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በአጠቃላይ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን የሚያቀላጥፍና ውጤታማ በሆነ መልኩ ዘርፉን መምራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ስምምነቱ የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንስቲቲዩቱ በስምምነቱ መሰረት የሚቀርቡለትን ፕሮጀክቶች በፍጥነት በማልማት በተያዘላቸው ጊዜ ለማቅረብ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም