በኦሮሚያ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ለማደራጀት የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ስማርት የመማር ማስተማር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ ፈርመውታል።  

ስምምነቱ ትምህርት በዲጂታል ታግዞ የሚተገበርበትን የስማርት መማር ማስተማር  እንዲካሄድ ይረዳል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በትምህርት ዘርፉም እንዲተገበር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ትምህርትን በዲጂታላይዜሽን የታገዘ እንዲሆንና ስማርት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ ዛሬ የመግባቢያ ሥምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በ8 አዳሪ ትምህርት ቤቶችና በ33 ልዩ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 82 ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን አሟልቶ ለማቅረብ የተደረገ ሥምምነት መሆኑን ተጠቁሟል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው: ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የትምህርት መስኩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በመሆኑም ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱን ጥራት ያለው ፍትኃዊና አካታች  የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም