በዓድዋ የተገኘውን አንጸባራቂ ድል ሀገራዊ የልማት ግቦችን በማሳካት መድገም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዓድዋ የተገኘውን አንጸባራቂ ድል ሀገራዊ የልማት ግቦችን በማሳካት መድገም ይገባል
ሐረር ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በዓድዋ የተገኘውን አንጸባራቂ ድል ትውልዱ አንድነቱን የበለጠ በማጠናከርና ሀገራዊ የልማት ግቦችን በማሳካት ሊደግመው እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ተናገሩ።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሐረሪ ክልል ደረጃ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡
አያቶቻችን በጠንካራ አንድነትና መስዋዕትነት ሉዓላዊ ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ ትውልዱም ተባብሮ ሀገሩን ማበልጸግ ይጠበቅበታል
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በወቅቱ እንደገለጹት፤ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል የተገኘ አንጸባራቂ ድል ነው።
የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት የተረጋገጠበት የአንድነት ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ የአሁኑ ትውልድም አንድነቱን በማጠናከር ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መረባረብ አለበት ብለዋል።
በበዓሉ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ ጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ኮሎኔል ሀሰን ሰዒድ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ለመላው አፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ድል እየተከበረና እየተዘከረ የመጣ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ገልጸው፤ ለወደፊቱም የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ ይቆያል ብለዋል።
ድሉ በመላው የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተባበረ ክንድ የተመዘገበ ነው ያሉት ኮለኔል ሀሰን ድሉን ሀገራዊ ልማትና ብልጽግናን በማረጋገጥ ማክበር ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት በማስከበርና ሌሎች በሀገሪቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ትንኮሳ በመመከት በጋራ በመቆም ማክበር ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በፓናል ውይይት በተከበረው በዓል ላይ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች፣ የፌዴራልና የክልሉ ፖሊስ አባላትና ሌሎች የጸጥታ አካላት፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የቀድሞ የጦር አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡