ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት በአፍሪካ የነጻነት ትግል ታሪክና ለዓለም ሰላም ዘብ በመቆም ግንባር ቀደም ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት በአፍሪካ የነጻነት ትግል ታሪክና ለዓለም ሰላም ዘብ በመቆም ግንባር ቀደም ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በሰለጠኑበት ኮልፌ ፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የተሰየመው የመታሰቢያ ሙዚየም ተመርቋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖሊስ ምስረታ 117 ዓመታትን ያስቆጠረ ከአፍሪካ ቀዳሚው ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ለአፍሪካ የነፃነት ትግል የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸው፤ የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አባት የሆኑትን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ አሰልጥኗል ብለዋል።

ኔልሰን ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ ትግልን ለመቀላቀል እ.ኤ.አ በ1962 በኢትዮጵያ ለወራት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ለመሰልጠን የመረጡት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና የዓለም ጥቁር ህዝቦች ምልክት በመሆኗ ነው ብለዋል።

ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያውያን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች መሰልጠናቸውን ጠቅሰው፤ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔ፣ መቶ አለቃ ፈቃዱ ወንድም ከአሰልጣኞች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ እውቀትና ልምዱን በማካፈል ለደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ነጻነት ታሪክ ቀረጻ ላይ ተሳትፎ እንዳላት ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ይሄውም የኢትዮጵያ ፖሊስ ተቋም የላቀ ሙያዊ ስነ-ምግባሩንና ሀገራዊ ሀላፊነቱን የተወጣበትን መንገድ እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ሙዚየም በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም