ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ተግባር ይጠናከራል
ደሴ ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች አካባቢዎች ለህክምና ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ በመሆኑ እድሉን ለመጠቀም የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንኑ በተመለከተም የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለጹት፤ የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግ፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል በማጠናከርና ግብዓትን በማሟላት ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ክትትልና ቁጥጥር ስኬታማ ተግባር አከናውናለች
ለዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በሌሎች የክልል ከተሞችም ግዙፍ ሆስፒታሎች እየተገነቡ ሲሆን የውስጥ ግብዓታቸው እንዲሟላ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታት ዘርፉን በማሳደግ ኢትዮጵያን የህክምን ቱሪዝም ማእከል ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ በዓይን፣ በጥርስ፣ በአንጎል፣ በመካንነትና በሌሎች የሕክምና ዘርፎች ላይ አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ህክምና እያገኙ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት።
ለዚህም ለአቅም ግንባታ ስራ ትኩረት በመስጠት የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ውጭ ሔደው በስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በተመረጡ ሆስፒታሎችም ዘመኑ የደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው አገልግሎት እንዲሰጡ ዘመናዊ የሕክምና ግብዓት እንዲሟላላቸው እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
መሰረታዊ የሕክምና መሳሪያዎችንና መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በተደረገው ጥረትም 40 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
እስከ ቀጣዩ ዓመት የሀገር ውስጥ ምርቱን ወደ 60 በመቶ ከፍ በማድረግ ለዘርፉ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ዜጎች ወደ ውጭ ለሕክምና እንዳይሄዱና እንዳይንገላቱ ከማድረግ ባለፈ አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጥራት ያለው ህክምና እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የኩታበርና ሱሉላ ጤና ጣቢያዎች በአጋር አካላት ድጋፍ የደረጃ ማሻሻያ ከተደረገላቸው በኋላ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ይታወሳል።