በኢትዮጵያ የተጀመረው ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት ሁነቶችን በስኬት ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጀመረው ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት ሁነቶችን በስኬት ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የሰው አልባ /Smart/ የፖሊስ ጣቢያ አገልግሎትን በማስጀመር ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ሁነቶችን በስኬት የማስተናገድ አቅም መፍጠሯን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተያዘው የካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ዜጎች የፖሊስ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ታግዘው በተሻለ ፍጥነት የሚያገኙበት ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት ተገልጋዩ በቴክኖሎጂ ታግዞ ራሱን በራሱ በማስተናገድ ተደራሽ፣ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ የወንጀል አቤቱታዎችን ለማቅረብ፣ የትራፊክ አደጋዎችን ሪፖርት ለማድረግ፣ የትራፊክ ቅጣቶችን ለመክፈል የጠፉና የተገኙ ቁሳቁሶችን ለማሳወቅ እንዲሁም የቱሪስት ደህንነት አገልግሎት ለማግኘት ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዘመናዊ መልክ ከተቋቋመ 117 ዓመታትን ያስቆጠረ በአፍሪካ አንጋፋው ተቋም ነው፡፡
ከአንጋፋነቱ ባለፈ እንደ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ያሉትን በማሰልጠን ለአፍሪካ የነፃነት ትግል ሚናውን የተወጣ፤ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ የተደረገው ሪፎርም በሰለጠነና ብቁ የሰው ሀይል የተሟላ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች የታጠቀና በሎጂስቲክስ አቅሙ የዳበረ ተቋም መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በዓለም የተሻለ የፖሊስ አገልግሎት አፈጻጸም ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ሪፎርም መደረጉን በማንሳት፤ በተለያዩ ዘርፎች እስከ ሶስተኛ ዲግሪ/ፒ ኤች ዲ/ የሚያስተምሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መገንባቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም እስካሁን በነበሩት ትላልቅ የፖሊስ ሥምሪቶች ተጨባጭ ውጤቶች በማስመዝገብ አንጋፋነቱን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሰማራት አንቱታን ያተረፈ ስኬት በማስመዝገብ ለዓለም ሰላምና ደህንነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የተጀመረው የሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት የውጭና የሀገር ውስጥ ዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የፖሊስ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችልና የተጠቃሚዎችን የመረጃ ደህንነትና ምስጢራዊነት ለመጠበቅ የላቀ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀምም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የፈጠረው ብቁ የሰው ሃይል፣ የታጠቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የተሟላ ሎጂስቲክስ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሁነቶችን በስኬት ለማጠናቀቅ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡