ቀጥታ፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በካንሰር ምርምር ላይ የሚያተኩረውን የelse korner center fore cancer care (EKC 2) ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍን በመጠናቀቅ ሁለተኛውን ምዕራፍ ይፋ አድርጓል፡፡


 

ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን የሴቶችን የካንሰር ሕክምና አገልግሎት በየአካባቢው ተደራሽ ማድረግ፣ ስለ ጡት እና ማህፀን በር ካንሰር ግንዛቤን ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በዚሁ ወቅት፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት በቅድመ ጥንቃቄ መከላከል ይቻላል ብለዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉትን ማኅበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለመግታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡

መንግስት የበሽታዎቹን ስርጭት ለመግታት ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ባሻገር ሌሎች ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥንቃቄ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ክፍል አስተባባሪ ዶክተር አዳሙ አዲሴ በበኩላቸው፤ የካንሰር በሽታ በአፍሪካ ደረጃ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ይህንን ለመቅረፍ ኮሌጁ ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንና የኤልሳ ክሮነር የካንሰር ሕክምና ማዕከል ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የጤና ማጎልበትና በሽታ መከላከል ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በተለይ በእናቶች ላይ የሚከሰቱ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ለመቀነስ ትልቅ ሚና አለው።

ቀደም ሲል በተመረጡ ሆስፒታሎች ብቻ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት አሁን በፕሮጀክቱ አማካኝነት ወደ ጤና ጣቢያዎች ዝቅ እንዲል መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም