በአማራ ክልል የማህበራዊ ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው - ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የማህበራዊ ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው - ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር)
ደሴ፤ የካቲት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የማህበራዊ ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ 175 ሚሊዮን ብር ወጪ የኤም. አር. አይ. ህክምና ማሽን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ በሆስፒታሉ በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው ባለ አራት ወለል ሕክምና መስጫም ሕንፃ ተመርቋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ የክልሉን ሰላም በመጠበቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተለይም የጤና፣ የትምህርትና የሌሎችንም ማህበራዊ ተቋማት ደረጃን በማሻሻልና በማጠናከር የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው ዘመናዊ ህንጻ እና ድጋፍ የተደረገው ዘመናዊ ማሽን የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ የተሻለ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጤና ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማደራጅትና ደረጃቸውን በማሻሻል ጥራት ያለው ህክምና እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ ከማድረግ ባለፈ ዘመናዊ ግብዓትም እየተሟላ ሲሆን ለሆስፒታሉ የኤም. አር. አይ. ማሽን ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
ማሽኑ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ እንደነበረ ጠቁመው፣ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና ለመስጠት ሲፈለግ የውስጥ በሽታዎችን ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሀይማኖት አየለ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብዓት በማሟላት ጥራት ያለው ህክምና እንዲሰጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከአማራ ክልል በተጨማሪ ከአፋር እና ከትግራይ ክልሎች ለሚመጡ ዜጎችም ጭምር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ዛሬ የተመረቀው ህንጻም አገልግሎቱን የበለጠ በማቀላጠፍና በማሻሻል ጥራት ያለው ህክምና ለመስጠት እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።
በፕሮግራሙ የክልል፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።