የጤና ጣቢያ ግንባታው የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚደረግን የረጅም ርቀት ጉዞን አስቀርቷል - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ጣቢያ ግንባታው የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚደረግን የረጅም ርቀት ጉዞን አስቀርቷል - ነዋሪዎች
መተማ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በቀበሌያቸው የጤና ጣቢያ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚያደርጉትን የጉዞ እንግልትና ወጪን እንዳስቀረላቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻል ቁልፍ ተግባር ነው
የጤና ጣቢያ ግንባታው ለሕክምና አገልግሎት ረጅም ርቀት መጓዝን ከማስቀረት ባለፈ ጊዜና ጉልበታቸውን ለልማት እንዲያውሉ እንዳገዛቸውም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ በአቅራቢያቸው በተገነባው ጤና ጣቢያ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ለሕክምና አገልግሎት ወደ ገንዳ ውኃ ከተማ ይሄዱ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ዳርጎናል ብለዋል።
የቀበሌው ነዋሪ አየሁሽ ስመኘው እንደገለጹት፣ የጤና ጣቢያው በአቅራቢያቸው መገንባቱ ያለምንም እንግልት ፈጣን ሕክምና እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።
ቀደም ሲል ወደ ገንዳ ውኃ በመሄድ ይባክን የነበረ ጊዜና ገንዘብን በመቆጠብ ለልማት ሥራ ማዋል መቻላቸውን ተናግረዋል።
ሌላዋ ነዋሪ ስፍራሽ ጌጡ የጤና ጣቢያው ግንባታ የእናቶችና ህጻናትን ጤና ከማሻሻል አኳያ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በጤና ጣቢያው የሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ዝግጅትን አስመልክቶ የሚሰጠው ትምህርት ለህጻናት ጤናና ለተሻለ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ጅብሪል መርሻ፣ በዞኑ ካሉት 23 የጤና ተቋማት መካከል ዘንድሮ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ከገቡት ሁለቱ ጤና ጣቢያዎች አንዱ የአፍጥጥ ጤና ጣቢያ መሆኑን ገልጸዋል።
ጤና ጣቢያው ከሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች በተጨማሪ ከ120 በላይ ለሚሆኑ የሥነ-አእምሮ ሕሙማን ተገቢው ሕክምና መስጠቱንም ገልጸዋል።
ዞኑ ሰፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት የሚካሄድበት እንደመሆኑ የነዋሪውንና የሠራተኛውን ጤና መጠበቅ ለምርታማነት ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።