ቀጥታ፡

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ግጭቶችን በመፍታትና ፍትህን በማስፈን ረገድ ውጤታማ ሆነዋል

ጊምቢ ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ስራ የገቡ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ግጭቶችን በመፍታትና ፍትህን በማስፈን ረገድ ውጤታማ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል መነሻውን የገዳ ሥርዓት በማድረግ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህጋዊ መሰረት ኖሯቸው እየሰሩ ይገኛሉ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን  ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በእርቅ በመፍታት፣ እውነተኛ ፍትህ እያገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጸዋል። 

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና በመቀነስና ማህበረሰባዊ እሴትን በማጠናከር በኩል ውጤት እያስገኙ ነው

 

ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ለተለያዩ እንግልቶችና ወጪዎች ይዳረጉ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመግባባቶችን በአጭር ጊዜ በእርቅ በመፍታት፣ ፍትህ እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተመልክቷል።


 

በኢናንጎ 02 ቀበሌ በባህላዊ ፍርድ ቤት የቤተሰባቸውን የንብረት ውርስ ለማስከበር የመጡት ወይዘሮ ጣይቱ ኩመራ፤ ጉዳያቸውን ተቀባይነት ባላቸው የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በጥቂት ቀናት ውስጥ ማስፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ባህልና ወጉን ጠብቆ ችግሮችን በእርቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም አካላት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላው የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጉታታ ዲቢሳ በበኩላቸው፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የማህበረሰቡን እሴት ተከትለው የሚሰሩ በመሆናቸው የሀሰት ምስክርነትን በማስቀረት እውነተኛ ፍትህ እንዲሰፍን እያገዙ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጉዳይ ለማስፈጸም የነበረውን እንግልት በመቀነስ፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በአባገዳዎች አማካኝነት ፍትህ ሳይጓደል መፍትሄ ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል።

የቡና መሬት የወሰን ችግር አጋጥሟቸው ወደ ባህላዊ ፍርድ ቤት የመጡት አቶ ጫላ ቀነኣ፤ ጉዳያቸው በገዳ ሥርዓት መሠረት ውሳኔ አግኝቶ በእርቅ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ምስጋኑ ደገፋ እንደገለጹት፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ፍትህ እንዲያገኝ እያደረጉ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በዞኑ 481 ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በዞኑ ማህበረሰቡ ባህልና እሴቱን ጠብቆ አለመግባባቶችን በእርቅ እንዲፈታ ማስቻል እንዲሁም በህዝቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በማስቀረት ረገድ ትርጉም ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ምስጋኑ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም