ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ካስማና የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ካስማና የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ ነው
ባህር ዳር፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ካስማና የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ መሆኑን የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው ገለጹ።
በዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ያሳዩትን ጥንካሬና አንድነት ወጣቱ ትውልድ በልማት ሊደግመው ይገባል
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጋራ መስዋዕትነት ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን የነጻነትና የኩራት አርማ ነው።
ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ያለምንም ልዩነት ድል ማድረጋቸው በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያን ትልቅ ስነ-ልቦናዊ ስንቅ ሆኗል።
የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ክብር ሲደፈር በራሳቸው ስንቅና ትጥቅ መዝመታቸውን አስታውሰዋል።
ዓድዋ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ክንዳቸውን አስተባብረው የቅኝ ገዥዎችን የባርነት ቀንበር የሰበሩበት ታሪካዊ ድል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ፋና ወጊ መሆኑንና የኢትዮጵያውያን የአንድነት ካስማና የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የሀገርን አንድነት ለማጽናት ስለ ቀደመ ታሪክ ማወቅና ታሪኩን ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የዓድዋ ጀግኖች አባቶች በደማቸው ያቆዩትን ሀገር፣ የአሁኑ ትውልድ በዕውቀትና በሥራ በመትጋት የተሻለ ሀገር መገንባት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ክብር ከፍ ያደረገና የአፍሪካውያን የአንድነትና የሉዓላዊነት ምልክት ሆኖ ይጠቀሳል።