በጋምቤላ ክልል ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ተጠቃሚነት ይበልጥ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ተጠቃሚነት ይበልጥ ይጠናከራል
ጋምቤላ፤ የካቲት 18/2018 (ኢዜአ)፦ በክልሉ የጤና መድህን ስርዓቱን በማጠናከር ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ምክር ቤት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጤና መድህን አገልግሎቱ ዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ።
በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በአነስተኛ ወጪ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙና ጤናቸው እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎቱን ለማጠናከርና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ተጠናከሮ የሚቀጥል መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
የጤና መድህን አገልግሎቱን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወነ ለሚገኘው ስራ ስኬታማነት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዱዓለም በበኩላቸው የጤና መድህን አገልግሎት ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር አገልግሎቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ካልታሰበ የህክምና ወጭ በመታደግ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ከፍለው መታከም ለማይችሉ 17 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መቻሉንም ነው ያስረዱት።
በጋምቤላ ክልልም ለዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ዋና አላማም የአባላት ምዝገባና እድሳትን በማጠናከር ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የጤና መድህን አገልግሎት በክልሉ ከሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ በ13ቱ ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል።