የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመው የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ያስጠበቁበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመው የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ያስጠበቁበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመው የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ያስጠበቁበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ''ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ'' በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን የካቲት 23/2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡
የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፋና ወጊ እና የኢትዮጵያውያን የአንድነት ተምሳሌት ሲሆን ይህ ድል ዛሬም ድረስ ለሀገራዊ ልማትና ለሉዓላዊነት መከበር እንደ ትልቅ ስንቅ እየተጠቀሰ ይገኛል።
130ኛውን የዓድዋ ድል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል
ድሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከግል ፍላጎት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ማስቀደምን ያስተማረ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ይናገራሉ።
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ልማት ተመራማሪ የሆኑት ጌጤ ነገሪ፣ ጀግኖች አባቶቻችን የውስጥ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ጸንተው ሀገራቸውን ከወራሪ ነጻ ማድረግ ችለዋል ብለዋል።
በወቅቱ የሀገራችን ህዝቦች በሁሉም አቅጣጫ በጋራ ቆመው ባሳዩት ጥንካሬ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያነገበውን ወራሪ ኃይል ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳዩበት ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
ትውልዱ አሁን ላይ ተባብሮና ተስማምቶ በመስራት ታላቁን የህዳሴ ግድብና ሌሎች አንጸባራቂ የልማት ድሎችን ማስመዝገብ እንደቻለ ሁሉ አንድነቱን አጠናክሮ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ከዳር ማድረስ እንዳለበት መክረዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የዛሬው ትውልድ ከዓድዋ ጀግኖች በወረሰው ወኔ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እና የባህር በር የባለቤትነት መብትን ለማስመለስ መትጋት አለበት ብለዋል።
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ታሪኩ ራጋ ፤ ዓድዋ አባቶቻችን በአንድነት ሆነው ውድ ህይወታቸውን ከፍለው ኢትዮጵያን ያስከበሩበት የድል ታሪክ መሆኑን አስረድተዋል።
የዛሬው ትውልድም ታላላቅ ድሎችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ከነዚህ መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ መብራቴ ጊርግሶ፤ የዓድዋ ድል የሀገር ባለቤትነት ስሜት መገለጫ እና የኢትዮጵያዊነት ጽናት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል ጥቁር ህዝቦች በጋራ በመሆን ማንኛውንም ነገር ማሸነፍ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን አንስተው አሁን የውስጥ ችግሮቻችንን በንግግር በመፍታት ለብሔራዊ ጥቅም መቆም ይጠበቅብናል ሲሉም ገልጸዋል።
በታሪክ እና ህዝብ አስተዳደር ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሄዱት ብርሃኑ ሌንጅሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የአንድነትና ጥንካሬ ውጤት መሆኑን አንስተው በዚህ ዘመንም ድሉ በህዳሴ ግድብ የተደገመ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ አፍሪካኒዝምን በማጠናከር አለም በማንነት ላይ ያላትን የተንሸዋረረ እይታ መለወጥ የተቻለበትና ህዝቡ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ባሉት የጋራ ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ ከሰራ የማያሳካው ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በጋራ ቆመው ክብርና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቁበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን አስረድተዋል።
ትውልዱ እንደ አባቶቹ ብሔራዊ ጥቅሙን ለማስከበር የባህር በር ባለቤትነት ላይ አንድነቱን አጠናክሮ ሊቆም ይገባል ብለዋል።