ቀጥታ፡

በዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ያሳዩትን ጥንካሬና አንድነት ወጣቱ ትውልድ በልማት ሊደግመው ይገባል

 የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦በዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና ጠንካራ የአንድነት ስሜት ወጣቱ ትውልድ ሊያስቀጥለውና በልማቱ ሊደግመው እንደሚገባ በሲዳማ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አስታወቀ፡፡

130 ኛው የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ በመጪው ሰኞ የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመው የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ያስጠበቁበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት ነው

በሲዳማ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ የኋላእሸት ቸርነት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዓድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜትና አንድነት የተገለፀበት ነው፡፡

ወጣቱ ትውልድም በዓድዋ ድል የታየውን የሀገር ፍቅር፣ አንድነትና አይበገሬነት ሊያስቀጥለውና በልማቱም ሊደግመው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ኩራት፣ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ደግሞ የነጻነት ጮራ የፈነጠቀበት በመሆኑ መታሰቢያውን ስናከብር የቀደሙ አባቶችን አርዓያነት ያለው ተግባር በማስቀጠል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ልዩነት እንደሌላቸውና በሉዓላዊነታቸው እንደማይደራደሩ ያሳዩበት ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሀገር የምትገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን የገለጹት አቶ የኋላእሸት የትናንት አባቶች ያስረከቡንን ነጻ ሀገር በልማት ማሳደግና ቀዳሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም በኢኮኖሚ የዳበረች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት መንግስት የጀመራቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በመደገፍ የልማት አርበኛ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ማህበራቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቀንን በማስመልከት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ትውልዱን ማስተማር መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ አባል የሆኑት ወይዘሮ ገነት ለማ ናቸው፡፡


 

የዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ለሃገር ሉዓላዊነት የከፈሉት መስዋእትነት በደማቅ ቀለም የተፃፈበት መሆኑን ትውልድ በተገቢው ሊረዳውና ሊያስቀጥለው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ድሉ በመላ ኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉን ስናከብር ትምህርት በመውሰድ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል ለትውልዱ ጀግንነትን፣ አንድነትንና አብሮነትን ያስተማረ የጥቁር ህዝቦች ድል ሲሆን የሃገር ፍቅርና የሰንደቅ ዓላማ ክብር የተገለፀበት የጋራ ታሪክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም