ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ከቀደሙት አያቶቻችን የተቀበልነው የሀገር ፍቅር ምልክትና የጀግንነት ስንቅ ነው

ሐረር፤የካቲት 18/2018 (ኢዜአ) ፡-የዓድዋ ድል ከቀደሙት አያቶቻችን የተቀበልነው የሀገር ፍቅር ምልክትና የጀግንነት ስንቅ ነው ሲሉ የምስራቅ እዝ የሰራዊት አባላት ገለጹ። 

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ አባላት 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ ራስ እምሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ በፓናል ውይይት አክብረዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የሰራዊቱ አመራሮችና አባላት የዓድዋን በአል ስናከብር የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በጀግንነት ለመጠበቅ ዳግም ቃል በመግባት ነው ብለዋል።

ከእዙ አመራሮች መካከል ኮለኔል መላኩ ዘገዬ፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቆመው የሀገራቸውን ክብርና ሉአላዊነት ያስከበሩበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዓድዋ የአሁኑ ትውልድ ከቀደሙት የሀገር ፍቅርን፣ ጀግንነትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚማርበት ስለመሆኑ አንስተው፤ የዓድዋ ድል ከአያቶቻችን የተቀበልነው የሀገር ፍቅር ምልክትና የጀግንነት ስንቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የዓድዋ ድልን የተረከበው ትውልድ የህዳሴ ግድብን በመገንባት የልማት ድል አድራጊነቱን ማሳየቱን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋትና ልማቷን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን ሰራዊታችን አይታገስም ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

ሌሎች የእዙ አመራሮች ሻምበል ሂሩት እምዩ እና ሻለቃ ሀሮን ገርቢ፤ በአድዋ የተመዘገበውን የአሸናፊነት ደማቅ የታሪክ አሻራ በጀግንነት እንዲቀጥል ማድረግ የዚህ ትውልድ አደራና ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድል በመሰነቅ ለኢትዮጵያ ሰላም እድገትና ማንሰራራት በፅናት መቆማቸውን አረጋግጠዋል።


 

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ ሌተናል ኮለኔል መስፍን አባተ፤ የዓድዋ ድል አያቶቻችን በቅኝ ግዛት ስር እንዳንወድቅ መስዋዕት በመክፈል ያስረከቡን ታላቅ አደራ በመሆኑ ሁሌም እንዘክረዋለን ብለዋል።


 

የጀግኖች አርበኞች ተተኪ ትውልዶች ሆነን ለአገር ሉዓላዊነት መከበር መስዋእትነት አየከፈልን ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የፓናል ውይይቱን የመሩት  ኮሎኔል ደምሌ አማረ፤ የዓድዋ ድል የይቻላልና የአይበገሬነት መንፈስን በማህበረሰቡና በሰራዊቱ እንዲሰፍን አድርጓል።


 

ሰራዊቱም ከቀደምቶች በወረሰው ጀግንነት ሀገሩን በሁሉ መስክ ሳያስደፍር እንድትቀጥል ማድረጉን ገልጸው በዚህም አሁን የተመዘገበውን የልማት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም