ቀጥታ፡

በድሬደዋ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተደራሽነትና አገልግሎቶች ይጠናከራሉ - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ፣ የካቲት 19/2018(ኢዜአ):- በድሬደዋ ለተገልጋዩ ፈጣንና ተደራሽ የፍርድ አገልግሎት በመስጠት ወሳኝ ሚና እያበረከቱ የሚገኙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ይጠናከራሉ ሲሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

በድሬደዋ አስተደዳር  የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ምክርቤት የማቋቋምና ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች ዕውቅና የመስጠት ስነስርአት ዛሬ በይፋ ተካሂዷል።


 

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለዜጎች ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ጫና እያቃለሉ ናቸው።

የፍትህ አገልግሎቱ እንዲሻሻል እያከናወኑ ያሉትን አበረታች ተግባራት ይበልጥ ተቋማዊ ለማድረግ የሚመሩበት የህግ ማዕቀፍ በአስተዳደሩ ምክርቤት ፀድቆ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው  የምክርቤቱ መቋቋም ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል ።


 

የድሬደዋ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ በበኩላቸው የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት የአሰራር ስነስርአት ማህበረሰቡን ተደራሽ በማድረግ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝና ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር እያስቻሉ መሆኑን አንስተዋል።

ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚለያቸውን ድንበርና አሰራር በመለየት የሚፈለገውን ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግላቸው በማስታወቅ።

የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ባህላዊ ህጎችና እሴቶችን በመጠበቅና  የማህበረሰቡን መስተጋብር በማጠናከር  የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና እያቃለሉ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንት አቶ ነጂብ ኢድሪስ ናቸው።


 

በተጨማሪም የሃብትና የጊዜ ብክነትን በመከላከል ምርታማነት ይበልጥ እንዲጎለብት አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተሰጣቸው ዕውቅና በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ነው አቶ ነጂብ የተናገሩት።


 

የኃይማኖት አባቶችና ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ኡጋዞች፣ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመሰረተው የባህላዊ ፍርድ ቤት ምክርቤት አባላት መሆናቸውን በስነስርዓቱ ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም