ፖለቲካ
የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቀቀ
Jun 10, 2024 174
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 3/2016(ኢዜአ)፦የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መጠናቀቁን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ። ፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና ዕርቅ ማውረድ፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ በተመሰረተ ምህረት፣ በተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም በማካካሻ ስልቶች ላይ የተዋቀረ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አስታውሷል፡፡ በፖሊሲው መሰረት ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ተቋቁመው ሁሉንም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስተግበሪያ ስልቶች ስራ ላይ እስኪያውሉ ድረስ የትግበራ ምዕራፉን የመጀመሪያ ዙር ስራ የማስተባበር ሚናውን ለመወጣት የትግበራ ሂደቱን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጿል። በዚህም መሰረት በፖሊሲው የትግበራ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር የያዘ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል። በፍኖተ-ካርታው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአባልነት የሚሳተፉበት ጊዜያዊ እና ዘላቂ ተቋማዊ የቅንጅት አመራር ስርዓት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ፤ ስለ ሽግግር ፍትህ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል መካተቱን አንስቷል። ተመጋጋቢነት እና ተደጋጋፊነት፤ ተቋማቱን ለማቋቋም እና ከተቋቋሙም በኋላ ስራቸውን ስለሚሰሩበት ሁኔታ የሚደነግጉ የህግ ማዕቀፎች ስለሚዘጋጁበት ሁኔታ እና የተቋማቱን አቅም ለመገንባት ስለሚሰሩ ስራዎች የሚያትቱ ዝርዝር ተግባራት ተቀርጸው ተቀምጠዋል ነው ያለው፡፡ ፍኖተ ካርታው በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት የክልሎችን፣ የባህላዊ ፍትህ ስርዓቶችን፣ የተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሚና፣ ተሳትፎ እና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን በተመለከተ የሚተገበሩ ተጨማሪ እርምጃዎችን በውስጡ እንዲይዝ መደረጉንም አብራርቷል። በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕ “በሀገር ወይም በመንግስት መሪነት እና ህዝባዊ ባለቤትነት" መርህ የሚመራ ስርዓት እንደመሆኑ መጠን ፖሊሲውን ህዝባዊ ገፅታ ለማላበስ የፖሊሲውን አስፈላጊነት፣ ይዘት እና የትግበራ ሂደት በተመለከተ ሕዝቡ ያለውን እውቀት ለማሳደግ ስለሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ዝርዝር ተግባራት በፍኖተ ካርታው እንዲመላከቱ ተደርጓል፡፡ ከትግበራ ምዕራፍ ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት የቅንጅት አመራር ስርዓት ማቋቋሚያ ረቂቅ መመሪያ፣ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደመ- ተከተል ማብራሪያ ሰነድ መዘጋጀታቸውን ገልጿል። የአጋር ተቋማት ግንኙነት እና ትብብር ማንዋል እና የሽግግር ፍትሕ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዶች የተዘጋጁ ሲሆን ፖሊሲውን ወደ ተለያዩ ሀገር በቀል ቋንቋዎች የመተርጎም ስራው መጀመሩንም ጠቁሟል። የእንግሊዝኛውን ቅጂ የማዘጋጀት ስራው ከእርማት በስተቀር በአብዛኛው መጠናቀቁንም በመግለጫው አንስቷል፡፡ በዚህም መሰረት የፍኖተ ካርታውን ረቂቅ ሰነድ ጨምሮ በተዘጋጁት የማስተግበሪያ ሰነዶች ላይ የሚደረጉት ውይይቶች ሲጠናቀቁ የፖሊሲው ትግበራ ምዕራፍ ዋና ዋና ተግበራት መከናወን እንደሚጀምሩ አረጋግጧል፡፡  
የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል ለአዲስ ሰልጣኞች የስልጠና መክፈቻ ስነ-ስርዓት አከናወነ
Jun 9, 2024 164
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016 (ኢዜአ)፦ የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሠልጠኛ ማዕከል ለአዲስ ሰልጣኞች የስልጠና መክፈቻ ስነ-ስርዓት አከናውኗል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በፈቃደኝነትና በሞራል ሀገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል የመጡ ወጣቶችን የመሰረታዊ ውትድርና ስልጠና በመስጠትና በማብቃት የተቋሙን የሰው ሃይል ለማጠናከር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መምጣቱን ተናግረዋል። ሰልጣኞችም በስልጠና ቆይታቸው የሚገጥሟቸውን ውጣ ውረዶች በጥንካሬ በማለፍ ጠንካራ ጓዳዊ ዝምድናን በማጎልበት ለሀገር መከታ መሆን እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።   የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አበባው ሰይድ ሰልጣኞች አርዓያ ሆነው በመሠልጠንና ጥንካሬን ሙያዊ ብቃትንና የአዕምሮ ብስለትን በመፍጠር ከውስጥና ከውጭ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ትንኮሳዎችን በመመከት ዘመናዊ ሠራዊት የመገንባቱ ሂደት መደገፍ እንዳለባቸው፤ ብቁ ሆነው ሥለጠናውን ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። የማሠልጠኛ ማዕከሉ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ ሠልጣኞች በማሰልጠኛ ቆይታቸው የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በብቃት በመሰልጠን፣ በስልጠናው ሂደት የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በቆራጥነት ማለፍና በጠንካራ ወታደራዊ ዲስፕሊን ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
ወጣቶች የዕኩይ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለማክሸፍና ልማትን ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
Jun 9, 2024 219
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ በየአካባቢው የጸጥታ ችግርና በህዝብ ላይ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ዕኩይ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በማክሸፍ ረገድ የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከወጣት ለሰላምና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ወጣቶች በሀገራቸው ሰላምና ልማት ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና ሰጥቷል፡፡   የወጣት ለሰላምና ለልማት ማህበር ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት በሥራ ፈጠራና አቅም ግንባታ ዙሪያ ሥልጠና የሚሰጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ በኩል ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ የራሳቸውንና ህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ ስኬት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት ያመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሀብት ማፍራት፣ በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን በመፍታት እና የተዛቡ ትርክቶችን በማረቅ አርዓያ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶች በሰላምና ልማት ላይ በሚደረገው ምክክር የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት መድረክ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም ወጣቶች ጥያቄያቸውን በኃይል ሳይሆን በሰላማዊና በውይይት መፍታት እንደሚችሉ መግባባት በመፍጠር ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች የሸኔ ሽብር ቡድን እንቅስቃሴን በማክሰምና ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል። በተለይም በተሳሳተ መንገድ ወደ ሽብር ቡድኑ የገቡ ወጣቶች መንግስት ያመቻቸውን የሰላም ጥሪ በመጠቀም በይቅርታ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህም ባለፈ ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት በህዝቡ መካከል ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ድርጊት በማክሸፍ ረገድ ወጣቶች ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡   የወጣት ለሰላምና ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት ቦና ደበላ፤ ወጣቶች በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገለጸው፤ ወጣቶች በአስተሳሰብና በተግባር አንድነት ካልተቀየሩ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቢኒያም በለጠ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግና ቢል ጌት ካሉ ባለ ራዕይ ግለሰቦች መማር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰፊ የስራ አማራጮች መኖራቸውን ገልጸው፤ እነዚህን እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም መንግስት በቅድሚያ ለወጣቶች በቂ ክህሎትና ግንዛቤ እንዲፈጥር ጠይቀዋል፡፡ መንግስት በሚፈጥራቸው ምቹ ሁኔታዎች ለመጠቀም ደግሞ ወጣቶች ራሳቸውን ለስልጠና እና ለስራ በማዘጋጀት እና ባለድርሻ አካላትም ትብብራቸውን በማጎልበት ሀገርን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ከመንግስት ጋር በመቀራረብ ለሀገር ሰላምና ልማት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት ሽመልስ ኢንሰርሙ፣ ሻምበል ደቻሳ እና ተሬቻ ሆርዶፋ ሀገራዊ መግባባትና ልማትን ማምጣት በሚችሉ ጉዳዮች በንቃት እንደሚሳተፉ አንስተዋል፡፡ ወጣቶች የሀገር ኢኮኖሚና የሰላም የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸው፤ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሚፈቱት በውይይት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የሰላምና የልማት ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ከመንግስት ጎን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡ መንግስትም የወጣቶችን ጥያቄ በጽሞና በማዳመጥ ማወያየትና አቅማቸውን ለማሳደግ ተገቢውን ስልጠና መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በጅማ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ
Jun 9, 2024 147
ጅማ ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሃገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ ውይይት በጅማ ከተማ ተካሄደ። በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት ሀገር በብዙ ፈተና ውስጥ ሆና በርካታ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል ።   በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተሰሩ የግብርና ልማት ስራዎች አበይት ውጤት ያስመዘገቡ እንደነበሩ ገልጸው ይህንን ለማስቀጠል መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል። በቀጣይም በሙሉ አቅም በማልማት ከተረጅነት ለመላቀቅ የኢኮኖሚ አቅማችንን ለማጎልበት በትጋት እንሰራለንም ሲሉ አክለዋል ። በነባራዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝቡ ጋር በመመካከርና በመወያየት የሚነሱ ሀሳቦችን እና አስታያየቶችን በመቀበል ለተሻለ ልማትና አስተዳደር እንደሚሰራ አስታውቀዋል ። የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው “አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ በመሆኑ የማምረት እድሉን ለመጠቀም እየሰራን ነው” ብለዋል። የጅማ ዞን ከቡና አምራችነቱ በተጨማሪ የበጋ ስንዴን እና የክረምት ሩዝን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን በማምረት የሚታወቅ እንደሆነም አንስተዋል። የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው “ህዝባችንን የአምራችነትና አልምቶ የመጠቀም ባህልን በማዳበር እረገድ በትኩረት እየሰራን ነው” ብለዋል። ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና በመመካከር የተሻለ ለማልማትና ለማምረት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተቀብለን እንተገብራለን ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ሰላም የልማት መሰረት በመሆኑ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስራት አለበት ብለዋል። በውይይት መድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የጅማ ዞንና የጅማ ከተማ የስራ ሀላፊዎችና፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።      
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሔደ
Jun 9, 2024 119
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር በሚል መሪ ቃል የተሰናዳ ህዝባዊ ውይይት በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።   መድረኩን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በጋራ የመሩት ሲሆን በውይይቱ ላይ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።   ለውይይቱ እንደ ሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ግርማ አመንቴ ለኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና ራስን መቻል የዚህ ዘመን አርበኝነት ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።   በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ የሰጡት አቶ አረጋ ከበደ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ሃገራችን ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ ጉልበት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህ ጉዞ መሳካት ሁሉም ለሰላም፣ ለወንድማማችነትና ለአብሮነት ቅድሚያ በመስጠት የሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት አለብን ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን መሰረታዊ ለውጥ በዘላቂነት በማስቀጠል በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ማማ የማድረስ ሀገራዊ ራዕይን እውን ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሻሸመኔ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው
Jun 9, 2024 113
ሻሸመኔ ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ '' ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉአላዊነትና ክብር '' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በሻሸመኔ ከተማ እየተካሄደ ነው ። የውይይት መድረኩን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የብልፅግና ፖርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቡዱ ሁሴን (ዶ/ር) እና በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ በመምራት ላይ ናቸው። ውይይቱ እንደ ሀገር የተያዘውን ከተረጂነት ፈጥኖ የመላቀቅ እና ወደ ተጨባጭ ሥራ ለመግባት እንደሚያግዝ አቡዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገልጸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችም ላይ ገለፃና ማብራሪያ በመስጠት እንደ ሀገር የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠልም እንዲሁ። በውይይት መድረኩ ላይ ከክልል፣ ከምዕራብ አርሲ ዞንና ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት ተገኝተዋል። ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ ከምዕራብ አርሲ፣ ቦረና ፣ጉጂና ባሌ ዞኖች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ
የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ በላቀ ተሳትፎ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ
Jun 9, 2024 98
ሠመራ ፤ ሰኔ 2/2016 (ኢዜአ)፦ የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ በላቀ ተሳትፎ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ። "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር'' በሚል መሪ ሃሳብ የህዝባዊ የውይይት መድረክ በሠመራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። ህዝባዊ የውይይት መድረኩን በመምራት ላይ የሚገኙት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉና የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ናቸው።   በዚህ መድረክ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ይህ አጀንዳ የፌዴራልም የክልል መንግስታትም ዕቅድ መሆኑን አንስተው፤ የተረጂነት አስተሳሰብን እንደ አገር ማስወገድ ይገባል ብለዋል። ይህም የተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ ያስፈልገዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እነዚህን አጀንዳዎች መሠረት በማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል። በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዓሊ መሐመድ በበኩላቸው አገሪቷ ባጋጠሟት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያቶች አምራች የሆነው ጠንካራው ህዝባችን ተረጂ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል። የተረጂነት አስተሳሰብን ማስወገድ ይገባል ያሉት አቶ ዓሊ መሐመድ ይህን አስተሳሰብ ለማስወገድ ደግሞ መሰል ህዝባዊ የውይይት መድረኮቹ ፋይዳቸው የጎላ ናቸው ብለዋል።
የፌዴራልና ክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሐረሪ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ነው
Jun 9, 2024 76
ሐረር ፤ ሰኔ 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሐረሪ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ነው፡፡ በውይይቱም የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬን(ዶ/ር) ጨምሮ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጆክ፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር እና ሌሎች የክልሉ የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል። እንዲሁም አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ናቸው። ውይይቱ በዋናነት ከተረጂነት አስተሳሰብ በመውጣት ምርታማነትን ለማጎልበት ያለመ መሆኑም ተመላክቷል። በከተማው በሚገኘው የጨለንቆ ሰማዕታት መታሰቢያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ክብር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።
ከተመጽዋችነት አስተሳሰብ  በመላቀቅ  ለመጪው ትውልድ ምንዳ ማውረስ እንደሚገባ ተገለጸ
Jun 8, 2024 99
አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦ያሉን ጸጋዎች ወደ ሀብት እንዲቀየሩ ጠንክሮ በመስራትና ከተመጽዋችነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ለመጪው ትውልድ ምንዳን ማውረስ እንደሚገባ ተመላከተ። “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር” በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ዛሬው ዕለት ተደርጓል። በርካታ ፀጋዎችና በቂ የሰው ሃይል ይዘን የሰው እጅ ጠባቂ በመሆን ለዘመናት መኖራችን የሀገራችንን ክብር የማይመጥን በመሆኑ ተረጂነትን በቃ ልንለው ይገባናል በማለትም ተናግረዋል። አባቶች ለሀገራችን ሉዓላዊነት የህይወት ዋጋ በመክፈል በጀግንነት ማለፋቸውንና ይህ ትውልድ ደግሞ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የአርበኝነት ታሪክን መጻፍ እንደሚገባው የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ እንድትል በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመለየትና በመጠቀም እንዲሁም ጠንክረን በመስራት ብልጽግናዋን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል። ለዚህም ከ38 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት፣ ሰፊ የውሃ ሃብት፣ ማዕድናት፣ የቱሪዝም ሃብቶችና ሌሎች በርካታ ፀጋዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የጀመሯቸውን የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ የከተማ ግብርና፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና ሌሎች ተጨባጭ ለውጥ የታየባቸው ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ኃላፊው ገልጸዋል።   የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ተረጂነት፣ ልመናና የሰው እጅ መመልከት አስቀያሚና የማይመጥነን እንዲሁም የሚያዋርድ መሆኑን ገልጸዋል። ክልሉ ያለውን ሰፊ ጸጋ በመጠቀም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች በተመዘገቡባቸው መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል። ''ለዘመናት አሳንሶ ከሚያሳየን የተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የሥራ ባህላችንን ማጎልበት ይገባናል'' ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ተፈራ ኦይቻ ናቸው።   የህዝቡን የልማት ተሳትፎ በማጎልበት ከተረጂነት መውጣትና የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል። ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ እያንዳንዳችን የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ የተሻለች ሀገርን ለልጆቻችን ማውረስ ያስፈልጋል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በውይይቱ ላይ የተረጂነት አስተሳሰብ መንስኤዎች፣ የሚያስከትለው ጉዳትና መፍትሄዎቹ ላይ ከሁሉም ማህበራዊ መሠረት የተውጣጡ አካላት ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ሚናቸውንም ለመወጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።  
ከድህነት ለመውጣት ጠንክረን ልንሰራ ይገባል
Jun 8, 2024 102
ጋምቤላ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦ተረጅነትንና ልመናን በመጸየፍ ከድህነት ለመውጣት ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ። "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር " በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል። ሚኒስትሩ በውይይት መድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የተረጂነትና የልመናን አስተሳሰብ በመጸየፍ በምግብ እራስን ለመቻልና የሀገርን እድገት ለማፋጠን ጠንክሮ መስራት ይገባናል ብለዋል። ከተረጅነትና ከድህነት ለመውጣት በቤተሰብ ደረጃ እንደ አባወራና እማወራ ዝግጁ በመሆን ከአመራሩ ቁርጠኝነት ጋር ተዳምሮ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስወገድ እንደሚቻል ተናግረዋል። ጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በማልማት ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚተርፍ መሆኑን ገልጸዋል። እያንዳንዱ የክልሉ ነዋሪ ተግቶ መስራቱን ከቀጠለ እራሱ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ወደትርፍ አምራችነት የሚሸጋገርበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን አመልክተዋል። መንግስት በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።   ተረጅነትና ልመና የህዝብንና የሀገርን ክብር የሚያጎድፍ በመሆኑ ልንጸየፈው ይገባል ያሉት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዓለሙ ናቸው። ከተረጅነትና ድህነት ለመውጣት ህዝቡ የስራ ባህሉን በማጎልበት ጠንክሮ መስራት እንደሚበቅበት ተናግረዋል። ከውይይቱ ተሳፊዎች መካከል አቶ ተሰማ ናደው በሰጡት አስተያየት፤ እንደ ጋምቤላ ያለማዳበሪያ የሚለማ ድንግል መሬት ይዘን የተረጅነት አስተሳሰብ መያዛችን ተገቢ አይደለም ብለዋል። በመሆንም ተረጅነትና ድህነትን ለማስወገድ የስራ ባህላቸውን በማጎልበት መስራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል። ብንሰራ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት አለን ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ታታ አዴንግ ናቸው ። ከመድረኩ ያገኙትን ግብዓት በመውሰድ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ጋትዊች ጋች በበኩላቸው፤ አብሮነትን በማጠናከር ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ ላይ ከሁሉም የክልሉ ወረዳዎችና ዞኖች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።      
ዜጎችን በማሳተፍ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ ነው - ሰላም ሚኒስቴር   
Jun 8, 2024 98
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡- ዜጎችን በሀገራዊ ጉዳይ በማሳተፍ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለፁ። ሀገር አቀፉ ''ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም'' የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ሊያካሂድ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል። የሰላም የሩጫ ውድድሩ የሰላም ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጨምሮ የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የሚካሄድ ነው ተብሏል። የሩጫ ውድድሩ በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በከተማ አስተዳደሮችና በክልል ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህም ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀው መርኃ ግብር፤ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሩጫ ውድድሩ ዜጎችን በማሳተፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ አብሮነትን በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት የተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል። በሩጫ ውድድሩ ዜጎች የእርስበርስ ግንኙነትንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል። ስፖርት የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት እሴት የሚንፀባረቅበት መሆኑን በመግለፅ፤ ሰላምን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረትም ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው የጠቆሙት። ዜጎችን በአገራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በውይይትና በንግግር የመፍታት ባህል እንዲያድግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ዜጎች በሀገራዊ ጥቅምና እሴት የተቀራረበ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በመርኃ-ግብሩ የተሳተፉ የክልል ባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ ተወካዮች ስፖርት ከአካል እንቅስቃሴ ባለፈ ለሰላምና ለልማት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል። የሰላም የሩጫ ውድድርም ሀገራዊ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ የሩጫ ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። በስፖርት ማህበረሰቡ ያለው የመተባበርና የመደጋገፍ አቅም ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናከር ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል። የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች የሚካሄደው የሰላም የሩጫ ውድድር በሰላም ተከናውኖ ውድድሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልፀዋል። በውድድሩ ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱም ተገልጿል።      
ታንዛኒያ በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ታጠናክራለች  
Jun 8, 2024 109
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡-ታንዛኒያ በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ የአገሪቱ የመከላከያና ብሔራዊ አገልግሎት ሚኒስትር ስቴርጎሜና ላውረንስ ተናገሩ። ሚኒስትሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ታንዛኒያና ኢትዮጵያ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ያላቸው ታሪካዊ ትብብር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል። ሁለቱ አገራት በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሥምምነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንም አስታውሰዋል። ታንዛኒያ በቀጣናው እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብሯን እንደምታጠናክር ገልፀዋል። በሰው ኃይል ልማት ትብብር ኢትዮጵያ የታንዛኒያን ሙያተኞች በማሰልጠን ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ትልቅ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ሚኒስትሯ ገልፀዋል። የሁለቱን አገራት የሰላምና ጸጥታ ትብብር መስክ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ታንዛኒያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናግረዋል። ሚኒስትሯ ከመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጋር በዚህ ሳምንት መወያየታቸው ይታወሳል።    
የምግብ ሉዓዊነትን በማረጋገጥ ህዝብን ከድህነት ማላቀቅ የመንግስት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ ነው- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
Jun 8, 2024 92
ጎንደር ፤ ሰኔ 1/2016 (ኢዜአ)፡- የምግብ ሉዓዊነትን በማረጋገጥ ህዝብን ከድህነት ማላቀቅ የመንግስት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተተገበረ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር’’ በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል፡፡ በዚህ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ተረጂነትንና ተመጽዋችነትን ማስቀረት ይገባል፡፡ ሀገራችን የኢኮኖሚ እቅሟን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና የልማት ጸጋዎች ቢኖሯትም ያላደገ የስራ ባህል ስር ለሰደደ ድህነት ዳርጎን ቆይቷል ብለዋል፡፡ ድህነትን ኋቀርነትንና ጉስቁልናን ለትውልድ ሳናወርስ ሀገራዊ አቅምን በማሳደግ ልመናንና ተረጂነትን የሚጠየፍ ትውልድ ግንባታ ላይ አበክረን መስራት አለብን በማለት ተናግረዋል፡፡ ድህነትና ተረጂነት ለሰላም እጦትና አለመረጋጋት አስተዋጽኦ አለው ያሉት በመድረኩ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ እርስቱ ይርዳው ናቸው፡፡ መንግስት በሚቀጥሉት ዓመታት ሰፋፊ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞችን ተፈጻሚ ለማድረግ አቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የተፈጥሮ ውሃን፣ መሬትንና የሰው ጉልበትን አቀናጅቶ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል። የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የስራ እድል ፈጠራና የከተማ ግብርና ዋነኛ የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ድርቅን በራስ አቅም የመቋቋም ብቃትን የማሳደግ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡   የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ነው፡፡ የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሙላት ሞገስ በበኩላቸው፤ ድህነት አንገት የሚያስደፋና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ በመሆኑ መንግስት ድህነትን ለመቀነስ እንዲቻል የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች ህዝቡ የሚደግፋቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ''ከጦርነትና ከግጭት ድባብ በመውጣት የእድገትና የብልጽግና አውድ ወደ ሆነው የኢኮኖሚ ልማት ህዝብ ፊቱን እንዲያዞር ዛሬ የተጀመረው መድረክ በእጅጉ ጠቃሚ ነው'' ያሉት ደግሞ አቶ አምሃ ኤልያስ ናቸው፡፡ በምክክር መድረኩ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ከጎንደር ከተማና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።        
የአገሪቱን  እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ተግተን  መሰራት አለብን
Jun 8, 2024 82
ጋምቤላ፤ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፡-በአገሪቱ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በማልማት ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ተግተን በቅንጅት መስራት አለብን ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ። ''ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር'' በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው። ሚኒስትሩ በመድረኩ ፤ ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የልማትና የብልፅግና ጉዞውን እውን ለማድረግ ተግተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል። መንግስት በአገሪቱ ያሉትን የልማት አቅሞች አሟጦ በመጠቀም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የተፈጥሮ ፀጋዎችን አልምቶ በመጠቀም ከድህነት ለመላቀቅ ተቀናጅተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።   በተለይም ባለፉት ዓመታት የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። የውይይት መድረኩ በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አዳምጦ ምላሽ ለመስጠት የሚኖረው ፋይዳም የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚል የመወያያ ፅሁፍ በማቅረብ ላይ ናቸው።    
በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ማበረታታት ይገባል 
Jun 8, 2024 138
ሶዶ፤አርባ ምንጭ ሰኔ 1/2016(ኢዜአ)፦ "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶና በአርባ ምንጭ ከተሞች እየተካሄደ ነው። በወላይታ ሶዶ የውይይት መድረኩን የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማና የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤለማ አብበክር እየመሩት ነው ።   በወቅቱም አቶ ፈቃዱ እንደገለፁት፤ ውይይቱ በአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችና እምቅ አቅሞችን በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ማበረታታትን ያለመ ነው። ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ አውቀን ልንጠቀምባቸው ይገባል ያሉት አቶ ፈቃዱ በነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል ብለዋል። በህዝባዊ ውይይት መድረኩ ላይ በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የማህበራዊ መሰረቶች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።   በተመሳሳይም ይኸው መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ውይይቱን የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ከከተማው ከሁሉም ማህበራዊ መሠረት የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ህዝባዊ ውይይቱን እየተሳተፉ ነው። መድረኩ የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ የምግብ ዋስትናንና አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑም ተገልጿል። ለዚህም የውስጥ አቅምን በማጎልበት ፀጋዎችን በአግባቡ መጠቀምና የብልጽግና ራዕይን ማረጋገጥ ተኪ የሌለው ጉዳይ እንደሆነም ተመላክቷል።  
በደሴ፣ ባህር ዳርና ጎንደር ከተሞች ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ  ነው
Jun 8, 2024 290
ደሴ/ ባህር ዳር/ ጎንደር ፤ ሰኔ 1 /2016(ኢዜአ)፡- "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በደሴ፣ባህርዳርና ጎንደር ከተሞች እየተካሄደ ነው። በደሴ ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማና የወረዳ አመራር አባላት ተገኝተዋል። እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።   የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ፤ ሁላችንም አንድነታችንን ጠብቀን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል። ከምንም በፊት ለዘላቂ ልማትና እድገት ወሳኝ ለሆነው ሰላም በታላቅ ትብብርና ቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል። በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የአመራር አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች ጋር እየተወያዩ ነው።   በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ከተረጂነት መላቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በቅርብ ዓመታት ተጀምረው ስኬታማ የሆኑትን የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር እንዲሁም የስንዴ ልማትን አጠናክሮ በማስቀጠል ተረጂነትንና ልመናን ማስቀረት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ርስቱ ይርዳው፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዲሁም ከጎንደር ከተማ አስተዳደርና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው፡፡   በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማውና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች ፣የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም