በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ህዝብን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ህዝብን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና መዋቅሮች እውቅና ተሰጥቷል።

እውቅናው የተሰጠው ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የ2017 ዓ/ም የፓርቲና የመንግስት የስራ አፈፃፀም እና የ2018 ዓ/ም እቅድ አቅጣጫ የግምገማ መድረክ ማምሻውን ሲጠናቀቅ ነው።

በወቅቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም መስክ በሚባል ደረጃ ስኬታማ ስራ ማከናወን ተችሏል።

ይህንን ጥንካሬ ለማስቀጠል በግምገማው የጥንካሬ እና የድክመት መንስኤዎችን በጥልቀት መርምረን በመለየት አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል።


 

በመሆኑም በአዲሱ በጀት ዓመት የጥንካሬ መሠረቶችን በማስፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረው እንቅስቃሴ በየደረጃው ያለው አመራር በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት ለመስራት እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።

እውቅናና ሽልማት ላገኙ መዋቅሮች የእንኳን ደስ አላችሁ በማለትም ባገኛችሁት ስኬት ሳትኩራሩ፣ ለበለጠ እንድትተጉ ሲሉ አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በበኩላቸው በክልሉ መንግስት ሽልማትና እውቅና የተሰጠው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስራን በጥራትና በብዛት መፈፀም የቻሉ አካላትን ለማበረታታት ነው ብለዋል።

በተለይ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በሁሉም የልማት መስኮች፣ በፀጥታና በመልካም አስተዳደር፣ በገቢ አሰባሰብና በተለያዩ ኢኒሼቲቮች ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች ካላቸው መዋቅራዊ አደረጃጀት አኳያ እርስ በእርሰ እንዲወዳደሩ ጥረት መደረጉንም ገልፀዋል።

እውቅናና ሽልማቱ የተሻለ የሰሩትን ለማበረታታትና የአፈፃፀም ክፍተት ያለባቸው ደግሞ እንዲያስተካክሉ ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎችና ወረዳዎች፣ ዞኖች፣ ለከተሞችና የክልል ሴክተሮች እውቅናና ሽልማት መሰጠቱን አመልክተዋል።

ይህም እውቅና በየደረጃው የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ጠንካራ መዋቅር ለመገንባት መነሳሳትንና የውድድር መንፈስን ለማጎልበት ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም