በሲዳማ ክልል እየተመዘገበ ላለው ለውጥ የክልሉ ምክር ቤት ሚናውን በመወጣት አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው-አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል እየተመዘገበ ላለው ለውጥ የክልሉ ምክር ቤት ሚናውን በመወጣት ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ ገለጹ።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡


 

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እንደገለጹት በክልሉ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች እየተመዘገቡ ባሉ ውጤቶች ላይ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ አካላትን የሥራ አፈጻጸም ከመከታተል ባለፈ እስከ ታችኛው መዋቅሮች በመውረድ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚገመግም ተናግረዋል ፡፡

በተለይ የካፒታል ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ የመገምገም እንዲሁም በአስፈፃሚ ተቋማት ላይ ድንገተኛ ክትትል የማድረግ ሥራ ምክር ቤቱ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።

በዚህም ቀደም ሲል የካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ ይታይ የነበረው የመጓተት ችግር እየተፈታ መምጣቱን አመልክተዋል።

የፍትህ ስርዓቱን ለማጠናከር የሲዳማ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የሆነው "አፊኒ” በተደራጀ መንገድ እንዲመራ አዋጅና ሕጎችን በማውጣት ህብረተሰቡ ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዐት በተጨማሪ እንዲጠቀምበት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዳኝነት ሥርዐቱን በተሻለ ዕውቀት እንዲመሩም ከ568 ቀበሌያት ለተውጣጡ የባህል መሪዎች ሥልጠና መሰጠቱንም አፈ ጉባኤዋ ጠቁመዋል።


 

በክልሉ በዓመት ለሁለት ጊዜ ህዝባዊ ፎረሞች እንደሚደረጉ የገለጹት ወይዘሮ ፋንታዬ፣ በእዚህም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ለይቶ በመገምገም ለመፍትሄው እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።  

ለአብነትም በዳራ ቀባዶ ሆስፒታል ተፈጥሮ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ህዝባዊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት በተወሰደ እርምጃ ለማስተካከል መቻሉን ጠቅሰዋል።

በኦዲት ግኝት 22 ሚሊዮን ብር የባከነ ገንዘብ ለማስመለስ እንደተቻለ ጠቁመው፣ 450 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በአሰራር ብልሽት ይባክን የነበረ ገንዘብም ለማስተካከልና ለማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

በጉባኤው ያለፈው የምክርቤቱ ስብሰባ  ቃለ ጉባኤ የፀደቀ ሲሆን የምክር ቤቱ የበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው ፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም