የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው - ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው - ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና፣ በጤና ሳይንስ፣ በቢዝነስ እና በኃብት አስተዳደር እንዲሁም በሌሎች የትምህርት መርኃ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መንግሥት ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታ እንዲሁም ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ማፍለቅና ማምረት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በእውቀት፣ በዓላማ እና በሙያዊ ክህሎት የታነጹ ጀግና የሰራዊት አባላት እና ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን እያፈራን ነው ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲም የሰለጠነ የሠራዊት አባላትንና ሲቪል አመራር በማፍራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሠራዊቱን የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ብቃት ለማላቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሙያተኞች እያፈራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሀገርና ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ስራ መሥራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፥ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎትን በማስፋት እንዲተገብርም ተናግረዋል።
በዘመናዊ የሠራዊት ግንባታ ሂደት እውቀትና ቴክኖሎጂ መሠረታዊ መሆኑን አንስተው ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ከዚህ አኳያ አመርቂ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተመራቂዎች በታማኝነት፣ በቅንነትና በስነምግባር ሀገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ፤ ዩኒቨርሲቲው በእውቀትና በክህሎት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የመከላከያ ሰራዊቱን የተልዕኮ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሀገርን የሚያሻግሩ ሥራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የመከላከያን የሰለጠነ የሰራዊት ግንባታ በማገዝ ላይ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ለመተካት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ስራዎችን በመሥራት ላይ መሆኑን አክለዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች መካከል ሀምሳ አለቃ ንጋቱ ሞላ እና ፍራኦል ጉተማ በተማሩት የሙያ መስክ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ምርምር እና በጤናው ዘርፍ የሠራዊቱን አቅም ለማጎልበት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
አስር አለቃ ሃብታሙ ሊበን በበኩሉ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ፥ እውቀቱን ለሌሎች የሰራዊቱ አባላት ለማካፈል ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡
በምርቃት መርኃ ግብሩ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በ2025 ከአፍሪካ አምስት ምርጥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቋል።