ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳም ተስፋዬ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ለቀጣናው ሀገራት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ትብብርን ይበልጥ ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም  ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ለመጡ ዲፕሎማቶች ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።


 


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳም ተስፋዬ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው ትብብርን ይበልጥ ለማጎልበት እየሰራች ነው ብለዋል።

ቀጣናው ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ ስደትና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ሌሎች በተናጥል ሊፈቱ የማይችሉ ችግሮች ያሉበት መሆኑን አንስተዋል።

ተግዳሮቶችን ለመፍታት ብዙ ጠቃሚ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም በቀጣይም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ስልጠናው ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ጥበቦችን እና ቁርጠኝነት የሚጠናከርበት አንዱ ጠቃሚ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የቀጣናውን ትብብር ማጠናከር እና በህዝቦች መካከል ጥልቅ መግባባት መፍጠር በስልጠናው መርሃ ግብር ከተቀመጡ ተልዕኮዎች መካከል መሆኑንም ተናግረዋል።

 በጋራ ክልላዊ ተግዳሮቶች ላይ የትብብር መድረክን መፍጠር፣ በአፍሪካ ቀንድ ገንቢ ተሳትፎን ማበረታታት እና ማሳደግ ሌላኛው ዓላማ እንደሆነ አክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስልጠና ክፍል ዳይሬክተር ጀነራል መላኩ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ ስልጠናው በጋራ በሆኑ ቀጣናው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ስልጠናው በፓን አፍሪካኒዝም፣ ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶችን በጋራ መጠቀምና  ሰላም ማስከበር ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን የመጡ ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ እንዳለ  ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም