የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ አዋጆችን እና ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ አዋጆችን እና ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ) ፡- የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን የተለያዩ አዋጆችን እና ሹመት በማፅደቅ አጠናቀቀ ።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል ።
አዋጁ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ፣ በሰራተኞች መካከል ፍትሀዊና አዎንታዊ ውድድር እንዲኖር ሚና ያለው እንደሆነ ተገልጿል ።
በሌላ በኩል የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስፈፃሚ አካላት ማቋቋሚያ ፤ ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል ።
አዋጁ በሀገርና በክልል ደረጃ ያለውን ለውጥ መነሻ በማድረግ ተቋማት ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎቶች ተደራሽና አካታች እንዲሆኑ ብሎም ተግባራቸውን በቅንጅት እንዲፈፅሙና ሀብትን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል ።
ምክር ቤቱ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አደረጃጀት ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅንም እንዲሁ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል ።
ይህም ፖሊስ የተሰጠውን ሕገመንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችለው እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሀዋሳ ከተማ መዋቅራዊ የውስጥ አደረጃጀትን መልሶ ለማዋቀር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም አፅድቋል ።
በዚህም የሀዋሳ ከተማ በአምስት ክፍለ ከተሞችና 26 ቀበሌዎች የሚዋቀር መሆኑ ተመለክቷል።
ምክር ቤቱ የቀረቡለትን የተለያዩ ሹመቶችን አፅድቋል ።
በዚህም መሰረት ፡-
1/አቶ ቢኒያም ሰለሞንን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፣
2/አቶ ገነነ ሹኔን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፣
3/ አቶ ፍቅረየሱስ አሸናፊን የክልሉ የመሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ
4/ አቶ ዳዊት ዳንጊሶን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ የሾመ ሲሆን፤ ተሿሚዎቹ በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቀርበው ቃለ መሀላ ፈፅመዋል ።የምክር ቤቱ ጉባኤ መረሃ ግብሩን በዚሁ አጠናቋል።