የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡
ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት፣ የ2018 በጀት ዓመት አቅጣጫ፣ የ2018 ረቂቅ በጀት እና የተለያዩ አዋጆች ላይ በመወያየት አጽድቋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረቡ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎችን ሹመት አጽድቋል።
በዚህም መሰረት አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ መኮንን ያኢ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ ኦሊያድ ስዩም የከተማ ቦታ ማስለቀቅ ጉዳዩች እና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።
ምክር ቤቱ የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ውሳኔ፣ አስፈላጊነት፣ ዝርዝር ይዘት፣ ተሳትፎ፣ የሚያስገኘው ሃብት፣ የሚፈታው ችግር እንዲሁም ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ተገቢነት ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት፦
- ከአዲስ አበባ የባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተልዕኮዎች የቱሪዝም ዘርፉ ለብቻው የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ሆኖ ለከንቲባ ፅህፈት ቤት ተጠሪ በመሆን እንዲቋቋም፣
- የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ቢሮን ከትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት ጋር እንዲዋሃድ፣
- የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ፅህፈት ቤት ከህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር እንዲዋሃድ እና
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አንድ ተግባር በከፊል ለውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ማስተላለፍ ላይ የቀረበውን ማሻሻያ አዋጅ ምክር ቤቱ በመሉ ድምፅ አፅድቋል።