ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎችና መራጮች ምዝገባ በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲካሄድ የሚያስችል አሰራር ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ለሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎችና መራጮች ምዝገባ በምርጫ ጣቢያዎች በአካል ተገኝተው ከማካሄድ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ጭምር እንዲካሄድ አሰራር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎች ስያሜዎች ደረጃቸውን የጠበቁና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑም እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ሰባተኛው ዙር አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ለማካሄድ ከህግ-ማሻሻል ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው።

በፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዳደርና የምርጫ ስርዓት ማስፈጸሚያ አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥናት መካሄዱንም ነው ያነሱት።

ቀደም ሲል በተካሄዱ ምርጫዎች ሲካሄድ የነበረው የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር እንዲካሄድም አሰራር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ በምርጫ ጣቢያ በአካል ተገኝተው ከመመዝገብ በተጨማሪ ስማርት ስልክና ታብሌትን በመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ለማካሄድ አማራጮች ተዘጋጅተዋል።

የማሻሻያ አዋጁ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አካቶ እንዲፀድቅም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን አስታውቀዋል።

የምርጫ ጣቢያዎችን ለመራጮች ምቹና ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የምርጫ ጣቢያዎች ስያሜ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲሰየም ዝግጅቶች መደረጋቸውን ነው ሰብሳቢዋ የተናገሩት።

በዚህም የምርጫ ጣቢያዎችን የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ መሰረተ ልማትና ግብዓት የማሟላት ሥራ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ቦርዱ በአገራዊ ምርጫው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያዝ እየሰራ መሆኑን ነው ሰብሳቢዋ የገለጹት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች መርሃ ግብሮቻቸውን ለመራጩ ህዝብ በተገቢው መንገድ እንዲያቀርቡ በቂ ስልጠና መስጠቱንም እንዲሁ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመረጃ ላይ የተመሰረተ መራጭ እንዲኖራቸው መርሃ ግብሮቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ይፋዊ መድረክ በቅርቡ እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም