የጋራ ትርክትን በመገንባት የጋራ መፃኢ እጣ ፈንታን ለመወሰን በሚደረገው ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ ነው-አቶ ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክትን በመገንባት የጋራ መፃኢ እጣ ፈንታን ለመወሰን በሚደረገው ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ ነው-አቶ ዛዲግ አብርሃ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦የጋራ ትርክትን በመገንባት የጋራ መፃኢ እጣ ፈንታ ለመወሰን በሚደረገው ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል ጋር በመተባበር በትርክትና በአገር ግንባታ የጋዜጠኝነት ሚናን የተመለከተ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው ስልጠና የኢዜአ የማዕከልና ክልል ቅርንጫፍ ቢሮ ኃላፊዎችና ሰራተኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ስለትርክት ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ የትርክት ኃይልና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በስልጠናው ትርክት ማንነትን ለመቅረፅ፣ሰዎችን ለማነሳሳት፣ ባህልን ለማሻገር እንዲሁም ውሳኔ ለመወሰን የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል።
ትርክት ዓለምን የምናይበት መነፅር መሆኑ ጠቅሰው፤ ትርክቷን የዘነጋች አገር እንዴት መነሳት እንዳለባት አታውቅም ብለዋል።
ትርክት ማንነትን የሚቀርፅ መሆኑና አገር የሚወለደው በጋራ ትርክት እንደሆነም አቶ ዛዲግ ገልፀዋል።
የጋራ ትርክትን መገንባት የጋራ መፃኢ እጣ ፈንታን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ለጋራ ትርክት ግንባታ ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።