በዓመቱ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር መሰረት የጣሉ ሥራዎች ተከናውነዋል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በዓመቱ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር መሰረት የጣሉ ሥራዎች ተከናውነዋል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት ከተረጂነት ለመውጣት የተከናወኑ ሥራዎች የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር መሰረት የጣሉ ናቸው አሉ የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲው ሥራዎች ማጠቃለያ የግምገማ መድረክ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ፥ 2017 በጀት ዓመት በርካታ ሥራዎች የተከናወኑበት፣ የትጋት እና የስኬት ዓመት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ፓርቲውን በሰብዓዊና በቁሳዊ ሃብት ለማጠናከር፣ በዘመናዊ መረጃ ለማደራጀት እንዲሁም ገዢ ትርክትና ቅቡልነትን ከማረጋገጥ አንጻር የተከናወኑ ሥራዎች ስኬታማ ናቸው ብለዋል።
በአስተሳሰብ፣በአደረጃጀትና በአሰራር የተዋሃደ ፓርቲ ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች ስኬታማ እንደነበሩ ጠቁመው፥ በዚህም የፓርቲውን 2ኛ መደበኛ ጉባዔና 5ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተቀናጀ መንገድ ማክበር ተችሏል ማለታቸውን የዘገበው ኤፍ ኤም ሲ ነው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን በትኩረት መሰራቱን የተናገሩት አቶ አደም፥ በዚህም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል፡፡
በንቅናቄ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ እና ሕዝቡ አካታች ሀገራዊ ምክክር ላይ እንዲሳተፍ በመደረጉ የምክክር ሒደት በተሳካ መንገድ መቀጠሉን አስገንዝበዋል፡፡
ገዢ ትርክትና ቅቡልነት እንዲረጋገጥ በተከናወነው ሥራ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ አዎንታዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ድሎችን ማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ ሕዝቡን በማሳተፍ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡