በኢትዮጵያ የዳበረና የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን አቅም መገንባት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የዳበረና የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን አቅም መገንባት ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዳበረና የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚና የኔዘርላንድስ መልቲ ፓርቲ ዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በመግባቢያ ስምምነቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማዳበር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አመራርና አባላትን አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላትን አቅም ማጎልበት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ማዘጋጀት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ከዚህ አኳያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋርም መስራቱ በዕወቀት የሚመራ አመራር ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን አቅም ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ የልህቀት አካዳሚው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
ለዚህ ደግሞ አካዳሚው በአገር በአቀል ዕውቀት የታገዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስልጠና መመሪያና የአመራር ልማት ግንባታ እቅድና ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
የኔዘርላንድ መልቲ ፓርቲ ዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ይነበብ ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ የመድብለ-ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ እየተገነባ ላለው ዴሞክራሲ ስርዓት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ከልህቀት አካዳሚው ጋርም በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በዛሬው ዕለት መፈራረማቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ጠንካራ የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓት በመገንባት ሂደት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳትንት ዛዲግ አብረሃ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በዚህ ረገድ ተቋማቱ በኢትዮጵያ የዳበረና የተረጋጋ የመድብለ-ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የተፈራረሙትን ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ አቅማቸውን አሟጠው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።