በራስ ፀጋ የምግብ ሉዓላዊነትን እና ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በራስ ፀጋ የምግብ ሉዓላዊነትን እና ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል

ድሬደዋ፣ ሐምሌ 09/2017(ኢዜአ ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በራስ ፀጋ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት እና በፓርቲ ትብብር የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት እና የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮች፣ ሚኒስትሮች እና የየክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከተረጅነት የመውጣት ጥረት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ረገድና ሌሎችም ጉዳዮችን በመዳሰስ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና የተመዘገቡ ውጤቶችን በተመለከተ በስፋት ውይይት ተደርጓል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ ለዜጎች በውጭና ሀገር ውስጥ የስራ እድል በማመቻቸትና በመፍጠር ረገድ የተሳካ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲኖር በማድረግ ዜጎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለሀገር ከፍታና ብልፅግና መረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከስራ እድል ፈጠራም ባለፈ በሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተረጂነት ለመውጣት እና በራስ ፀጋ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በፓርቲና በመንግስት ትብብር የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አንስተዋል።
በመሆኑም የተገኘውን ውጤት በማስቀጠል በተያዘው በጀት ዓመትም የላቀ አፈፃፀም እንዲኖር የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ልማትና እድገት ማሳለጥ መቻሉን አንስተዋል።
የገበያ መረጋጋት እንዲኖር በመስራት የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ በስፋት ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።