መገናኛ ብዙሃን ሀገርን የሚገነቡ ተሻጋሪ ትርክቶች ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው - አቶ ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ሀገርን የሚገነቡ ተሻጋሪ ትርክቶች ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው - አቶ ዛዲግ አብርሃ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ሀገርን የሚገነቡ ዘመን ተሻጋሪ ትርክቶችን የመቅረጽ ሚናቸውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት እንዳለባቸው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) አመራሮች እና ጋዜጠኞች ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።
አቶ ዛዲግ መገናኛ ብዙሃን መረጃን ከማቅረብ ባሻገር መሰረታዊ ለውጥን የሚያመጡ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ሀገርን ለመገንባትና ዜጎችንም ለጋራ ሀገራዊ ግብ በአንድነት እንዲቆሙ የሚያስችሉ የይዘት ስራዎች ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቅሰው የግንባታ ሂደቱን ከማሳለጥ አኳያ ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ጋዜጠኞችም ከዕለት ደራሽ ዜና ባለፈ አዎንታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር ይዘት ሰርቻለሁ ወይ? በሚል ራሳቸውን በመፈተሽ ዘላቂነት ላላቸው ጉዳዮች ትኩረት መስጠትና ራሳቸውን ማብቃት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
መገናኛ ብዙሃን ችግር ነቃሽ ብቻ ሳይሆኑ መፍትሄ አፍላቂ መሆን ይገባቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም የጋዜጠኝነት ገንቢ ስራ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ዜጎች ላይ ተስፋን የሚጭሩ እና ብርሃን የሚያሳዩ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ድልድይ ሰዎችን እንደሚያገናኘው ሁሉ ትርክት የሰዎችን አዕምሮ ያገናኛል ያሉት ፕሬዝዳንቱ መገናኛ ብዙሃና የጋራ ትርክት ላይ በማተኮር ሀገር እና መንግስት ተቀራርበው እንዲሰሩ ምቹ መደላልድል መፍጠር እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ዘመን ተሻጋሪ የሚሆኑ ትርክቶችን በመቅረጽ፣ የህዝብ ድምጽ በመሆን እና ተቋማትን በማጠናከር ረገድ ጋዜጠኞች ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
በተለይም ዜጎችን ትክክለኛ እና እውነተኛ መረጃ በማስታጠቅ እና ንቃተ ህሊናቸውን በማሳደግ ለሀገራቸው ጥቅም እና ፍላጎት እንዲቆሙ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ጋዜጠኛው ለፈተናዎች እና ለችግሮች እጅ ሳይሰጥ በአይበገሬነት በመስራት ሀገርን የሚገነቡ እና ትውልድን የሚቀርጹ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባት አሳስበዋል።