የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ብቁ ሰራዊት ከመገንባት በተጓዳኝ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን እየፈጠረ ነው - ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ብቁ ሰራዊት ከመገንባት በተጓዳኝ ዘመኑን የዋጁ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እየፈጠረ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው በምህንድስና፣ በጤና ሳይንስ፣ በቢዝነስ፣ በኃብት አስተዳደር እና በሌሎች የትምህርት መርኃ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃ መርኃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ፤ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ወታደራዊ፣ ሲቪል እና የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በእውቀትና በክህሎት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እያፈራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የመከላከያ ሰራዊቱን የተልዕኮ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሀገርን የሚያሻግሩ ሥራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የመከላከያን የሰለጠነ የሰራዊት ግንባታ በማገዝ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሰራዊቱን ስምና ዝና በሚመጥን መልኩ የተዋቀረ ሲሆን ከመማር ማስተማር ስራዎች በተጓዳኝ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችና ሌሎች ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት ከውጭ የምታስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ለመተካት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ስራዎችን በመሥራት ላይ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ተመራቂዎች ባገኙት እውቀትና ከፍተኛ ክህሎት ሀገራቸውን በብቃት ማገልገል እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በ2025 ከአፍሪካ አምስት ምርጥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም