ከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማትን ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ በማካፈል ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማትን ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ በማካፈል ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አሶሳ፤ሐምሌ 6/2017 (ኢዜአ)፦ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ በማካፈል ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአመራር ለአመራር ግንኙነትና ልምድ ልውውጥ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ በማካፈል ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማም በህብረተሰቡ ተሳትፎ እና በአመራሩ ቁርጠኝነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ተሞክሮን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ዘላቂ እና የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው መሠራት እንዳለባቸውም ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በልማቱ ሂደት የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ህብረተሰቡ ለራሱ መሆኑን ማስገነዘብ እና የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የሥራ እንቅስቃሴን የጎበኙት ከንቲባዋ፥ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይር እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጋት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ባለሃብቶች በልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር የልማት አሻራቸውን እንዲያሳርፉም በትብብር መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሶሳ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በክልሉ የልማት ሥራዎች ላይ እያደረጉት ለሚገኘው ድጋፍ አመስግነዋል።
ከከተማ አስተዳደሩ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የክልሉን የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ለማሳደግ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።