ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ 82 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ 82 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በፑንትላንድ የሚንቀሳቀሰው የአይ ኤስ የሶማሊያ ክንፍ በተለያዩ ሀገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመስፋፋትና የሽብር ቡድኑን ሴሎች ለመመስረት የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ የመረጃ ስምሪትና ጥናት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የአይ ኤስ የሶማሊያ ክንፍ በኢትዮጵያ የሽብር መረብ ለመዘርጋት የሚያደርገውን ሙከራ በተመለከተ ከጅምሩ በመረጃና በማስረጃ ተደግፎ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጫው ያስታወቀው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ፤ የሥጋት ደረጃውን በተመለከተ በየጊዜው ባከናወነው ግምገማ ተጋላጭነትን የሚያስከትሉና ወደ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሚያድጉ ተጨባጭ ግኝቶች መለየታቸውን ጠቁሟል፡፡

እንደ መግለጫው፤ የተከናወነውን ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ የማጠናቀር ሂደት ተከትሎ የሽብር ቡድኑ በፑንትላንድ አሰልጥኖ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሰማራቸው 82 ተጠርጣሪዎች ተለይተው ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ከቡድኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውና ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች መካተታቸውን በመግለጽ፤ በተለይ በዓለም-አቀፍ የሽብር ቡድኑ በመረጃ ክንፍ የተደራጁ እንዲሁም በፋይናንስና በሎጀስቲክ እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፋፋትና ምልመላ ለማከናወን የሃይማኖት ተቋማትንና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን ይጠቀማል ያለው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ የሕዝብን አንድነትና ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ ብሎም ለአመጽና ሁከት የሚያነሳሱ አስተምህሮዎችን ለማስፋፋት ሙከራ ሲደረግ እንደነበር በተጨባጭ ማስረጃ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ሃሮማያ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌ፣ ጅማና ሻኪሶ ከተማ ዙሪያ፤ በአማራ ክልል ከሚሴ አካባቢ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞንና ሃላባ ቁሊቶ ከተማ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና በሐረሪ ክልል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ ግለሰቦቹን ለመያዝ በተደረገው ስምሪት በየአካባቢው የሚገኘው ኅብረተሰብ ከደኅንነትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ያሳየው ተሳትፎ በመልካም አርዓያነት የሚጠቀስ እንደነበር የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ጠቁሟል፡፡

በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከተው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኅብረተሰቡም በየአካባቢው ሰላምን የሚያደፈርሱና ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት አንደ ሁልጊዜው ለሚመለከታቸው የደኅንነትና የጸጥታ አካላት ጥቆማ በማቅረብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም