በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት  መከናወናቸውን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የኦሮሚያ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ የስራ አፈፃፀም ግምገማ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ አፈጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማንን  ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዳማ መካሄድ ጀምሯል።


 

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለፁት በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል።

የክልሉ መንግሥት የአርሶና አርብቶ አደሩን እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ህይወት ለማሻሻልና ለመለወጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በስራ እድል ፈጠራ፣ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም በማዘመን፣ ገቢን በማሳደግና የአርብቶ አደሩን ህይወት መለወጥ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት መሰራቱን ጠቅሰዋል።

መድረኩ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም በጥልቀት የሚፈተሽበትና ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው ለ2018 በጀት ዓመት አቅጣጫ የሚያዝበት መሆኑን አመላክተዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርም  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ አበረታች ውጤቶችን በአዲሱ በጀት ዓመት በሙሉ አቅሙ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

"አዲሱ የበጀት ዓመት  ለህዝቡ ቃል የገባንበት ሁለንተናዊ የልማት መስኮች ለማሳካት በሙሉ አቅማችን የምንረባረብበት ዓመት በመሆኑ በየደረጃው ያለው አመራር ራሱን ማዘጋጀት አለበት" ሲሉም አክለዋል።

ለአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ብልሹ አሰራሮች፣ ሌብነት፣ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የጎጠኝነትና የጥቅም ጥገኝነት አመለካከቶችና አስተሳሰቦችን ለማምከን መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግሥትና በፓርቲ ስራ የተሻለ ተግባር የተከናወነበት ነው ብለዋል።


 

በዚህም ጠንካራ የመንግስትና የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ለመፍጠር አበረታች ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የቀበሌ አደረጃጀትና መዋቅር በመዘርጋት በተለይም ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።

በዚህም በክልሉ የተሻለ ሰላም በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ማከናወን የተቻለበት መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም