የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው በተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
አዋጁ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የሚቀርብ ማንኛውም ቅሬታ በምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚደነግግ ሲሆን የምርጫ ክልል አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ከዚህ በፊት ከህብረተሰቡ ይመደብ የነበረው ቀርቶ ቦርዱ አሰልጥኖ በሚመድባቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲተኩ የሚያደርግ ነው።
ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ አንድ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ የሚመለምለው አባል ከ5 ክልሎች የነበረ ሲሆን በተሻሻለው አዋጅ አንድ ፓርቲ አባላትን መመልመል ያለበት ከ7 ክልሎች ሊሆን እንደሚገባም በአዋጁ ተመላክቷል።
አንድ ፓርቲ ከመንግሥት ድጋፍ ለማግኘት ከ30 በመቶ ከሚሆነው አባሉ የአባልነት መዋጮ መሰብሰብ እንደቅደመ ሁኔታም ተቀምጧል።
በአዋጁ መሰረት ጥሰት ፈጽመው የተገኙ ፓርቲዎች እስከ አምስት ዓመት ድረስ ሊታገዱ የሚችሉበት ድንጋጌም ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል ነው።
በውይይቱ ከተሳተፉ መካከል የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ በምርጫ ጣቢያ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አይቶ ውሳኔ ይሰጣል የሚለው የአንቀጹ ክፍል ለአተገባበር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ ባንዲራ በላቸው እንደገለጹት፤ ፓርቲዎች 30 በመቶ መዋጮ እንዲያሰባስቡ የተቀመጠው ድንጋጌ ከነባራዊ ሁኔታ አኳያ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይ የሚለው ሊጤን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው በአዋጁ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ድንጋጌዎች ሊካተቱ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሌ በሰጡት ማብራሪያ በአዋጁ ፓርቲዎች 30 በመቶ ያህል መዋጮ ከአባላት ሊሰበሰቡ እንደሚገባ የተደነገገው ፓርቲዎች በመንግሥት በጀት ላይ ብቻ እንዳይመሰረቱና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።
አዋጁ አካል ጉዳተኞችንና ሴቶችን አካታች በሆነና ተሳትፏቸውን በሚያሳድግ መልኩ መቃኘቱን አንስተዋል።
የመንግሥት ሰራተኞች በምርጫ ውድድር ወቅት ደሞዛቸውን ይዘው እንዲሳተፉ መደረጉ ለፖለቲካ ምህዳሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ በሰጡት ማብራሪያ፤ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የሚነሱ ቅሬታዎች በምርጫ ጣቢያ ኃላፊ እንዲፈታ አቅጣጫ የተቀመጠው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ታልሞ መሆኑን አስረድተዋል።
እንዲያም ሆኖ ቅሬታዬ አልተፈታም የሚል ማንኛውም አካል ጥያቄውን በየደረጃው የሚያቀርብበት አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው በህዝባዊ የውይይት መድረኩ የተነሱ ሀሳቦች ለአዋጁ ውሳኔ ሀሳብ የሚረዱ ግበዓቶች የተገኙበት ነው ብለዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ ምክክር ላይ የፓርቲዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በበኩላቸው ፓርቲዎች የወጣቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአባልነት መዋጮን በተመለከተም ፓርቲዎች አባላቶቻቸውን ሊያበረታቱ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ለማዋል የጀመራቸውን ተግባራት ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠቁመው ፓርቲዎችም ይሄንኑ ስራ ሊደግፉ እንደሚገባ አመልክተዋል።