ቀጥታ፡

የሀመሯ እናት- የደስታ እንባ

የሀመሯ እናት- የደስታ እንባ

በጣፋጩ ሰለሞን (ከጂንካ) 

በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው ሐመር ወረዳ  የሐመር ብሔረሰብ ዘመን በተሻገሩ  ባህላዊ  ሥርዓቶች ይታወቃል። በዚህ አካባቢ ከሚዘወተሩትና በብዛት ከሚታወቁት ባህላዊ ሥርዓቶች መካከል “ኢቫንጋዲ እና ኡኩሊ” የተባሉ ባህላዊ ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ። 

“ኡኩሊ”በሐመሮች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን ለአቅመ አዳም የደረሰና ከብት ለመዝለል  ዝግጁ የሆነ የሐመር ወጣት የሚጠራበት የማዕረግ ስም ነው፡፡  “ኡኩሊ” ከብት በሚዘለልበት ዕለት ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ሥፍራ ላይ በቅርብም ይሁን በሩቅ ያሉ የወጣቱ ዘመዶች ተጠርተው የሚከናወን ባህላዊ ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል።

“ኢቫንጋዲ” ደግሞ በሐመሮች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን ትርጉሙም  “ኢቫን” ማለት “ ማታ”  ሲሆን “ጋዲ” ማለት ደግሞ “ጭፈራ” ማለት መሆኑ ይነገራል። ኢቫንጋዲ በአዝመራና በደስታ ወቅት በሥራ የደከመን አእምሮና አካል ለማዝናናት ሲባል የሚከናወንና የሀመር ወጣቶች በጉጉት የሚጠብቁት ባህላዊ ጭፈራ ነው። በዚህ ባህላዊ ጨዋታ ላይ የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች አምረውና ተውበው በጨረቃ ብርሃን ይጨፍራሉ። የኢቫንጋዲ ጭፈራ በሶስት ቀን አንድ ጊዜ በሐመር መንደሮች በምሽት ከጨረቃ ድምቀት ጋር አብሮ ይደምቃል። “በጨረቃ ብርሃን አየኋት በማታ ኢቫንጋዲው ቦታ” የተባለላቸው የሃመር ውብ ልጃገረዶችም ከጨረቃ ብርሃን ጋር ደምቀው የሚታዩበት ዕለት ይሆናል። 

በወጣትነታቸው በዚሁ ባህላዊ ሥርዓት ያለፉት የሀመሯ እናት- ወይዘሮ ባሎ ኡርጎ  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናት ናቸው።  በሐመር ወረዳ ዲመካ ከተማ  የሚኖሩት ወይዘሮ ባሎ፤ በደሳሳ ጎጇቸው ሲያገኙ በልተው ሲያጡ ደግሞ ኩርምት ብለው ያሳለፉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ያስታውሳሉ።

በደሳሳ ጎጆ እየኖሩ ዝናብ ሲመጣ የጎርፍ፣ ብርድና ዶፉ ስጋት ላይ ጥሏቸው እንደኖሩ ያነሳሉ፤ በበጋ ወራት ደግሞ የሚነፍሰው ነፋስና ሀሩሩ ጸሃይ ይፈትናቸው እንደነበር ይናገራሉ። 

ከእለታት አንድ ቀን ወጣቶችና ጎልማሶች ጭምር ሰብሰብ ብለው መጥተው “ቤትዎን በነፃ ልናድስልዎት ነው ሲሉኝ አላመንኳቸውም ይላሉ። የእውነታችሁን ነው አልኳቸው? አዎን ቤትዎን አፍርሰን ልንሰራልዎት ነው” ብለው አረጋገጡልኝ በማለት ሁኔታውን በደስታ እንባ ታጅበው ያስታውሳሉ።

በተባለው መሰረትም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤታቸው እድሳት ተጀምሯል። የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው ተገኝቶ ወይዘሮ ባሎን ባነጋገራቸው ወቅት “ሰው በሚያስፈልገኝ ጊዜ ሰዎች ሁነው የተገኙ ወገኖቼ ችግሬን ለመፍታት በአካል ተገኝተዋል፤ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የመኖርን ተስፋ እንድሰንቅ አድርገውኛል በማለት ደስታቸውን በእንባቸው ጭምር ታጅበው ገልጸዋል።

የሀመሯ እናት ቤታቸው በፍጥነት ታድሶ የሚረከቡ፣  በቀጣይም አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን የቤቱን እድሳት ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር አረጋግጠዋል። 

እንደ ወይዘሮ ባሎ፤ ያሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን  የማገዝና የመደገፍ ሃላፊነት አለብን ያሉት ሃላፊው፤  የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል ጎልቶ እንዲቀጥል ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል። 

የቢሮው የማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች ለወገኖቻቸውያላቸውን አለኝታነት በተግባር በማሳየታቸውም አመስግነዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፤ የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ ተቋማት፣ግለሰቦች፣ወጣቶችና  አዛውንቶች ሳይቀር የተሳተፉበት እና የበርካቶችን   ችግር መፍታት የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች  የወይዘሮ ባሎን  ቤት ለማደስ በመምጣታቸው አመስግነው፤ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሚሆን የመልካምነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በተያዘው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤቶችን ጨምሮ የዞኑን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ  በርካታ ተግባራት በመከናወን  ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በዞኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን  የመደገፍና ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን በስፋት የማከናወን ተግባር  በተጠናከረ መለኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም