ከጉርስ እስከ ውርስ የሚዘልቅ ሃብት

(በሳሙኤል አየነው - አርባምንጭ)-ከጉርስ እስከ ውርስ የሚዘልቅ ሃብት...

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በአንድ ሰው 40 ችግኝ" በሚል መሪ ሃሳብ በ2011 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በዚሁ መርሃ ግብር ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን የማኖር ጥረታቸውን ቀጠሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በተጀመረው የአረንጓዴ ኢንሸቲቭ የተራቆቱ አካባቢዎች ከማገገማቸው  ባለፈ የምግብ ሉአላዊነትን የማረጋገጥን  ድርብ አላማ ሰንቆ ለተከታታይ ሰባት አመታት ዘልቋል።

ኢትዮጵያዊያን በዘንድሮው መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መርህ በአንድ ጀምበር ብቻ 714 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ምንም ነገር ማሳካት እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል። 

ባለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞች ውጤትና  የዘንድሮውን  ተሳትፎ  የኢዜአ ሪፖርተር በአርባ ምንጭ እና አካባቢው ነዋሪዎችን አነጋግሯል።  

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ  አቶ ተዘራ ቀፃዮ፤የአረንጓዴ አሻራ  የተቆረጡ ዛፎችን በመተካት የተራቆቱ አካባቢዎችን ማልበስ ያስቻለና  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  እድል ፈጥሯል ብለዋል። የዚህ ስኬት ሚስጢሩ በተባበረ ክንድ መስራትና ለቁም ነገር ማብቃት በመቻላችን ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ሁሉን ከዳር ዳር ያነቃቃው ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት ተከታታይነት ያለው ሰፊ አሻራ እንድናኖር ያደረገ ነው ያሉት አቶ ተዘራ አሻራችንን እያኖርን፣ ከተፈጥሮ ጋር እየታረቅን እያለማንና እየተጠቀምን ከጉርስ እስከ ውርስ የሚዘልቅ ሃብት እየፈጠርን እንገኛለን ብለዋል።

በምድረ ገነትነት የምትታወቀው አርባምንጭ እና አካባቢው ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ ካባ እየለበሰ ይበልጥ ውብ እና ማራኪ እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል። ለአርባ ምንጭና አካባቢው ነዋሪዎች ችግኝ መትከልና መንከባከብ ልምድ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ተዘራ ለመጪው ትውልድ ምቹ አካባቢን የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል ብለዋል።

በአርባምንጭ ከተማ የ"ነህሚያ" እንስሳት እርባታና ማድለብ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ህዝቅኤል ኦሎባ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተፈጥሮን ከመጠበቅም ባለፈ ከድህነት የመውጫ ሁነኛ መፍትሄ እየሆነ መጥቷል ብሏል። የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአንድ በኩል ለደን ጥበቃና እንክብካቤ በሌላ በኩል ለእንስሳት መኖ እየዋለ ሲሆን በፍራፍሬ ልማትም የምግብ ዋስትና መሰረት እያኖረ መሆኑን አንስቷል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከኢትዮጵያም ባለፈ ከጎረቤት አገራት ጋር የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ያለ ስለመሆኑም አስረድቷል። በመሆኑም አሻራችንን በማኖር ሀገርን ማልማት፤ ለነገ የሚሆን ጥሪት ማኖርና የትውልዶች ውርስ እንዲሆን የሁላችንም ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብሏል።

በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሃሳብ አመንጭነት በ12 ዞኖች የአንድ ተራራ ልማት ኢኒሸቲቭ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በዚህም የከተማው ራስጌ ላይ የሚገኘው የጋንታ ተራራ ልማት ለአብነት የሚጠቀስ ሆኗል። በቅርቡ በዚሁ ተራራ ላይ አሻራቸውን ያኖሩት የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ የአርባዎቹ ምንጮች ቤትና የእምቅ ተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት የሆነው አርባ ምንጭ ይበልጥ እያማረበትና እየተዋበ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ የታዳሽ ሃይል እና የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያስታርቅ፣ ሀገርን የማልማትና የምግብ ዋስትና መሰረት መሆኑን ተናግረዋል። ከመጪው ትውልድ የተበደርነውን የተፈጥሮ ሀብት  በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ሀገር የማስረከብ ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

 የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የህዳሴ ግድብ ስኬት፣ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና አይ ሲቲ ጭምር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የጋራ ትርክት መገለጫዎችና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ተስፋ የተሰነቅንባቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣አከባቢጥበቃና ልማት ቢሮ ሃላፊ ግዛቴ ግጄ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ መሳካት በክልሉ ተጨባጭ ማሳያዎች መኖራቸውን አንስተዋል። የአረንጓዴ አሻራ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ለሌማት ትሩፋት የላቀ ትርጉም እንዳለው አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ተፈጥሮን ማልማትና የምግብ ዋስትና መሰረት ማኖር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በ12 ዞኖች በመንግስት፣ በግለሰብ፣ በማህበራትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 1 ሺህ 495 ችግኝ ጣቢያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በእነዚህም ለምግብነትና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የማፍላት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ በመትከል የማንሰራራት ዓላማ በመሰነቅ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት እየተጋን እንገኛለን ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም