ለለውጥና ስኬት የሚታትሩ እጆች - ኢዜአ አማርኛ
ለለውጥና ስኬት የሚታትሩ እጆች
(በማሙሽ ጋረደው)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የሚኖረው ወጣት ሀብታሙ ደስታ፤ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ከፍተኛ ትምህርት በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ተመርቋል። ሀብታሙ ከተመረቀበት ሙያ ባሻገር በአካባቢው መልካም እድሎችን በማጥናት ሰርቶ ለመለወጥና አግኝቶ ለማደግ ወሰነ። በዚህም መሰረት የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ከሚያመርት አንድ የግል ድርጅት ውስጥ በመቀጠር ስራ ጀመረ።
በድርጅቱ ውስጥ እየሰራ እና የሙያ ክህሎቱን እያሳደገ በሙያው የላቀ ብቃት እያካበተ መምጣቱን ያስታውሳል። በዚህም መሰረት ከሰባት ዓመት በፊት ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በ70 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በተመሳሳይ የእንጨት ስራ ጀመረ። በ70 ሺህ ብር የተጀመረው ስራም አሁን ላይ ካፒታሉ 10 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከ40 ለሚልቁ ወጣቶችም የስራ እድል የፈጠረ ሆኗል።
በሀገራችን የተለያዩ እድሎችና የስራ አማራጮች አሉ የሚለው ሀብታሙ፤ አንዳንዶች ስደትን የመጨረሻ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ በየአካባቢያቸው ሰርቶ የመለወጥ እድል መኖሩን ማየት አለባቸው ሲል ተናግሯል። በአካባቢው ሰርቶ መለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን አንስቶ እርሱ የተሰማራበት የእንጨት ስራ ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሷል።
የሀብታሙ ለለውጥና ስኬት የሚታትሩ እጆች ዛሬ ላይ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር አስችለዋል። ለመለወጥ ቁርጠኝነትና ጠንክሮ መስራት የግድ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ ተስፈኛ "ያለጥረት የሚገኝ ስኬት የለም" ሲልም ተናግሯል።
የሚያመርቷቸው የቤትና የቢሮ ዕቃዎች በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውን አንስቶ የራሱ እና የጓደኞቹ እንዲሁም የሌሎች የኑሮ ሁኔታ እየተቀየረ መሆኑን ገልጿል። በተለይም ወጣቶች በአካባቢያችን ያሉንን በርካታ አማራጮች ለይተን የማየትና የመጠቀም ውስንነቶቻችንን ማረም ከቻልን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መትረፍ የምንችልበት ምህዳር ተፈጥሯል፡፡'' ብሏል።
በከምባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ጆሬ ቀበሌ የሚኖሩት ሞዴል አርሶ አደር ሰለሞን ወልዴ፤ የጤና እክል ገጥሟቸውም ቢሆን እየታገሉ ከመስራትና ማምረት አልቦዘኑም። የህይወት መንገድ ብዙ ውጣ ውረድ የሚጠይቅ በመሆኑ ባለመስነፍና ተስፋ ባለመቁረጥ መስራት ይገባል የሚል እምነት አላቸው። በመሆኑም የእርሻ ስራ እና የዶሮ እርባታን ጭምር በማቀናጀት ከራሳቸውና ቤተሰባቸው የምግብ ዋስትና አልፈው ለሌሎችም የሚተርፍ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በመሆኑም በተለይ እምቅ ችሎታና ያልደከመ ጉልበት ያላቸው በመሆኑ በተለያዩ የልማት መስኮች መልፋት፣ መስራትና ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ። የኢትዮጵያ አየር ለመኖር የተመቸ፤ ለማምረት ተስማሚ በመሆኑ እድሉን ተጠቅሞ በቀላሉ ማደግና መለወጥ የሚቻል መሆኑን አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ፤ በክልሉ ያለውን እምቅ ኃብት በማልማትና በማምረት ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር ሰፊ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።በመሆኑም በተለይም ወጣቶች የመስራትና የፈጠራ ችሎታቸውን ተጠቅመው የሀገር ልማትና እድገት መሪ ተሰላፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። በክልሉ የስራ ዕድል የፈጠሩና የውጭ ምንዛሪ ወጪን የቀነሱ ኢንተርፕራይዞች መፈጠራቸውን አንስተው በመንግስት የብድር አቅርቦት፣ የግንዛቤና የህይወት ክህሎት ስልጠናን በመስጠት እገዛ የሚደረግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቻ ከ370 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አስታውሰው በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ለ400 ሺህ ሰዎች ስራ ለመፍጠር ታቅዷል ብለዋል።