ማኅበራዊ መሥተጋብርን የሚያጸናው - ቡሔ - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበራዊ መሥተጋብርን የሚያጸናው - ቡሔ

(በዮሐንስ ደርበው)
ሰዎችን ከንጥል እሳቤ እያፋቱ የወል አመለካከት በመትከል ማኅበራዊ መሥተጋብርን የሚያጸኑ ዕሴቶች ከሚገኙባቸው ሁነቶች መካከል በዓላት ይጠቀሳሉ።
ከእነዚህ በዓላት መካከል ደግሞ ሰሞኑን እየተከበረ ያለው ቡሔ (ደብረ ታቦር) አንዱ ነው፡፡
ቡሔ የቃሉ ፍቺ “መላጣ፣ ገላጣ” ማለት ነው ይላሉ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ቀሲስ አንድነት አሸናፊ።
በሀገራችን ክረምቱ አልፎ የብርሃን ወገግታ የሚታየው በዚሁ በዓል ወቅት አካባቢ ስለሆነ “ቡሔ” የተባለው በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ።
ይህም ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይናገራሉ።
ቡሔ ደብረ ታቦር እየተባለ እንደሚጠራም ያነሱት መምህሩ፤ "ቡሔ ከሚለው ይልቅ ደብረ ታቦር የሚለው መጠሪያ የተሻለ" ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡
የደብረ ታቦር በዓል ታሪካዊ አመጣጡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ከቁጥር 1 እስከ 9 ያለው ቃል መሆኑንም አንስተዋል።
በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 1 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራ በመውጣት በታቦር ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን ስለመግለጡ መገለጹን ጠቅሰው፤ በየዓመቱ ነሐሴ 13 የሚከበረው የቡሔ (ደብረ ታቦር) በዓል መነሻም ይህ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያንም ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ አድርጋ ትቀበለዋለች ይላሉ መምህር ቀሲስ አንድነት።
በዓላት በሐይማኖት ውስጥ ሁለት ዓላማ እንዳላቸው አስገንዝበው፤ አንደኛው ሰውና እግዚአብሔርን ማገናኘነት ሲሆን ሁለተኛው ሰውና ሰውን ማገናኘት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ስለዚህ በቡሔ በዓል ምክንያት ሰዎች ይገናኛሉ፤ ሰዎች ሲገናኙ ደግሞ በፍቅር፣ በእርቅ፣ ማዕድ በመጋራት ነው ይላሉ።
በተለይም በቡሔ በዓል ላይ የዝክር፣ ዳቦ የመስጠት፣ የጎረቤት መጠያየቅ፣ የተቸገረን የመርዳት፣ እነዚህን የመሳሰሉ ማኅበራዊ መሥተጋብርን አጽኚ፣ አቀራራቢ እና አሰባሳቢ ዕሴቶች እንደሚተገበሩ ያስረዳሉ፡፡
ቡሔ በርካታ ትውፊቶች እንዳሉት የሚናገሩት መምህር ቀሲስ አንድነት፤ ከእነዚህ መካከል ችቦ፣ ሙልሙል (ዳቦ)፣ ጅራፍ እና ዝክር የሚሉትን ጠቅሰዋል፡፡
የሚበራው ችቦ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የመግለጡ ምሳሌ ነው ብለዋል፡፡ ችቦው ብርሃንነትን ስለሚያሳይ ደቀመዛሙርቱ ብርሃኑን ዐይተው መውደቃቸውን ለማሳየት ነው ይላሉ፡፡
እንዲሁም ሙልሙል (ዳቦ) ደግሞ ደቀመዛሙርቱ በደብረ ታቦር በነበሩ ጊዜ ያን ለማየት የሄዱ ቤተሰቦቻቸው ይዘውላቸው ከመጡት ምግብ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።
በቡሔ የጮኸው ጅራፍም “አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ ይህን ስሙት ያለው” ምሳሌ ነው፤ የብርሃኑ መንጸባረቅ በደብረ ታቦር የነበረው ብርሃነ መለኮቱ ሲንጸባረቅ ብርሃን ታዬ ስለሚል የእዛ ምሳሌ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ከቡሔ ትውፊቶች አንዱ ዝክር መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የቡሔ በዓል በገጠር በአብነት ትምህርት ቤት የተማሪዎች ዝክር የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም ጎረቤት ለጎረቤቱ፣ ደቀመዛሙርት ለመምህሮቻቸው፣ ምዕመናን ለሌሎች ሰዎች ያካፍላሉ ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በየቤቱ ሂደው ቡሔን የሚያከብሩ፣ በዓሉ ሲከበር ምጽዋት እና ዳቦ የሚቀበሉ ልጆች ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ ሲገለጥ የሄዱ ወላጆች ልጆች ምሳሌ መሆኑን በመግለጽ፤ እነዚህ በሂደት የተላለፉልን ትውፊቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ቡሔ በልጆች፣ በወጣቶች፣ በሕብረተሰቡ ዘንድ መቀራረብን በማጠናከር ረገድ በጎ አስተዋጽዖ እያሳደረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለምሳሌ አንዳንዶች ልጆች ቡሔን በየዓመቱ ያስቀጥላሉ፤ ሌሎች ሲያደርጉ ዐይተው የሚቀላቀሉም አሉ፤ በዚህ ሂደት ነባሮቹ አዲሶቹን በመቀበል ግጥሙን ያስጠናሉ፤ ባህሉንና ትውፊቱንም እንዲጠብቁ ያስተምራሉ፤ በእነዚህ ሂደቶች አይዞህ በርታ እየተባባሉ መደጋገፍና መመሰጋገን አለ ነው የሚሉት።
አሁን አሁን በተለይ በከተማ አካባቢዎች ላይ ቡሔ በአግባቡ ሲከናወን አይስተዋልም ይላሉ። ልጆቻችን ማኅበራዊ ሚዲያ እና ኮምፒውተር ላይ ብቻ ተጣብቀው ባህላዊውን ነገር እየረሱት በመሆኑ ቡሔን በትክክል እንዲያውቁት ማድረግ ከወላጆች እና ማኅበረሰቡ ይጠበቃል ነው ያሉት።
እንደ መምህር ቀሲስ አንድነት ገለጻ፤ ልጆች ሆያሆዬ የሚሉት ለበዓሉ ክብርና ለስሜታቸው ነው። ምንም እንኳን ልጆች የገንዘብ ችግር ኖሮባቸው ባይሆንም ሆያሆዬ የሚሉት ከሆያሆዬ ጭፈራው በኋላ ገንዘብም ዳቦም እንደሚሰጥ ይናገራሉ።
ዳቦው ለትውፊቱ፤ ገንዘቡ ደግሞ ለልጆቹ ድካም እና የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ ስለሚሆን አንድም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እና ለመተጋገዝ መልካም አጋጣሚ ይሆናል ይላሉ።
ቃሉ “እርሱን ስሙት” ብሏልና በየደረጃው ከቤተብ እስከ ሀገር በመደማመጥ ከቡሔ (ደብረ ታቦር) መሰባሰብን፣ መግባባትንና መተሳሰብን መውሰድ እንደሚገባ ይመክራሉ።
መንግሥት ወይም ሕዝብ በሚሠራው ነገር ብቻ ሀገርን መገንባት እንደማይቻል ጠቅሰው፤ በደብረ ታቦር ክርስቶስ እንደሰጠው ትክክለኛ ምስክርነት ባልና ሚስት፣ ወላጆችና ልጆች፣ አሠሪና ሠራተኛ፣ መንግሥትና ሕዝብ፣ ትልቅና ትንሽ፣ ካህን እና ምዕመን ሁሉም እየተደማመጡና እየተግባቡ ለአንድ ዓላማ በጎ ዐሻራ ማኖር አለባቸው ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ ነው ሀገርዊ ፋይዳ ሊኖረው የሚችለው ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡