አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል- የልጃገረዶች የባህል ፈርጥ - ኢዜአ አማርኛ
አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል- የልጃገረዶች የባህል ፈርጥ

አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል- የልጃገረዶች የባህል ፈርጥ
በእንግዳው ከፍያለው
የነሃሴ ወር የልምላሜ ምልክት ነው። ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ የሚዘንበው ዝናብ ፍሬው የሚታየው በነሃሴ ወር ምድርን በሚያለብሰው ቡቃያና የሳር ልምላሜ ነው።
በዚህ ወር ሌት ከቀን የሚጥለው ዝናብ፣ በነፋስ የሚታገዘው ውሽንፍር፣ ውርጩና ቁሩ ሳይበግራቸው ልጃገረዶች ይሰባሰባሉ። የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓልን ለማከበር በእድሜ እኩያቸውና እንደየሰፈር ቅርበታቸው ቡድን ይመሰርታሉ።
ቡድን መመስረት ብቻ ሳይሆን “አሸንድዬ አኽ፤ አሸንዳ ሆይ፤ እሽ እርግፍ አትይሞይ፤…” የሚለውን የበዓሉን ማድመቂያ ጭፈራ መለማመድ ይጀምራሉ።
ከልምምዱ ጎን ለጎንም ለጆሯቸው ጉትቻ፣ ለአንገታቸው ድሪ፣ ማርዳ፣ ጠልሰምና ማሰሪያ የተለያየ ቀለም ያላቸው ክሮችን በመሰብሰብ ያዘጋጃሉ።
ለእጃቸው አምባር፣ ለእግራቸው አልቦና ሌሎች ጌጣጌጦችን ያፈላልጋሉ፤ ያሰባስባሉ፣ ያመቻቻሉ። ጌጣጌጦቹ ከእናቶቻቸው፣ ታላቅ እህቶቻቸውና ሌሎች ቤተሰቦችም ጭምር የሚሰበሰቡ ናቸው።
አዲስ የሚገዛ ገዝቶ ወይም ለክት የተቀመጠውን በማውጣት አልባሳት ያዘጋጃሉ። በበዓሉ ዋዜማ ለባህላዊ ጭፈራው ስያሜ መነሻ የሆነው “አሸንዳ” እየተባለ የሚጠራውን ረጃጅም ቅጠል ያለውን ተክል በማምጣት በወገብ ለማሰር በሚያመች መልኩ ተጎንጉኖ በጓሮ ጤዛ በያዘ ሳር ተሸፍኖ እንዲያድር ይደረጋል። ይህ የሚደረገው ጠንዝሎ እንዳይበጣጠስ ነው።
የጸጉር ስሬትም ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት፤ ጥሩ ጸጉር ሰሪ ማን እንደሆነች በመነጋገር ቀድመው ወረፋ ያስይዛሉ።
ለጸጉር ሰሪዋም በአይነትም ሆነ በብር ክፍያ ይዘጋጃል፤ ቀደም ሲል በነጻ እንደነበርም ይነገራል።
ይህ ሁሉ ዝግጅት የልጃገረዶች በዓል የሆነውን የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል በዓል በጋራ ለማክበር ነው።
ዝግጅቱን ለሚያይ ሰው “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ፤ ይበጣጠስ” የሚለውን የሀገሬውን ብሂል ለአሸንድዬ ያልሆነ ቀሚስ ... የተባለ ነው የሚያስመስለው።
ማህበረሰቡ በየቤቱ ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት እርስ በእርስ በመጠያየቅ የሚያጅብበት በዓልም ነው።
ድፎ ዳቦ፣ ሙልሙል ዳቦ፣ ጠላ፣ ጠጅና ሌሎች የምግብና የመጠጥ አይነቶች በየቤቱ ማዘጋጀት የተለመደ ነው።
ልጃገረዶች በየቤቱ እየዞሩ ሲጨፍሩ አንዱ ስጦታ ሙሉሙል ዳቦ ይሆናል ማለት ነው።
በዓሉ የሚከበርባቸው አካባቢዎችም በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ፣ ቡግና፣ መቄት፣ ግዳን፣ ቆቦ፣ ጉባላፍቶና መርሳ አካባቢዎች ሲሆን በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሁሉም ወረዳዎች በድምቀት ይከበራል።
በዓሉ ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር ነው። ከነሃሴ 16-21 በሚከበረው የበዓል ሳምንት ሴት ልጆች ከብት እንዲጠብቁ አይገደዱም፣ ሌላ ስራም እንዲሰሩ አይጠየቁም።
ምክንያቱም እለቱ ለእነርሱ የነፃነት ቀናቸው ነውና።
በዓሉ በልጃገረዶች ጭፈራ ብቻ የሚከበር ሳይሆን በታዳጊና ወጣት ወንዶች ጅራፍ ግርፊያና ማጮህ ታጅቦ የሚከበር ነው።
የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል በአካባቢው ባህል ተጨማሪ እሴት ያለው በዓል ነው። ለመተጫጨት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በዓልም ነው። በዓሉ ከመተጫጨትም ባለፈ ለሌሎች ማህበራዊ ትስስሮች ፋይዳው የጎላ ነው።
ልጃገረዶች በመሰረቱት ቡድን አምረው ለብሰውና ከጸጉር እስከ እግራቸው በተለያዩ ጌጣጌጦች ተውበው በዓሉን እያዜሙ ያከብራሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓሉ ከሰፈር ወጥቶ ትልቅ ትኩረትም አግኝቶ በየአደባባዮች መከበር ይዟል። በዚህም የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበ በአካበቢው ከሚገኙት ታሪካዊ የመስህብ ሃብቶች በተጨማሪ አዲስ የመስህብ ምንጭ እየሆነ መጥቷል።
ይህንን ድንቅና ታሪካዊ እሴት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኒስኮ/ በማስመዝገብ ኢትዮጵያን እንዲያስተዋውቅና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
የዘንድሮው የአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።
የበዓሉ አከባበር ባህላዊ እሴቱን አጉልቶ በማሳየት፣ ለሀገር ገጽታ ግንባታ፣ ለቱሪዝም ሃብት ምንጭነትና ለኢኮኖሚ ማንሰራራት የላቀ ፋይዳ እንዳለውም ይታመናል።