ቆሻሻን ወደ ሀብት በመቀየር የተለወጠ ቤተሰብ

አቶ ሔኖግ ዶንጋቶ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው።  በሚኖሩበት ሀዋሳ ከተማ 2005ዓም ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ቆሻሻን በእጅ ጋሪ መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ስራቸውን ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በኋላም በአንድ የአህያ ጋሪ ቆሻሻ  የመሰብሰብ ስራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ጠሉ።

በሂደትም ከባለቤታቸው ጋር ሆነው በተለያዩ ድርጅቶች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ የህክምና ተቋማት በመሄድ ቆሻሻን በመሰብሰብና በመለየት መልሶ ጥቅም እንዲሰጥ በማድረግ ስራውን አስፋፉ በኋላም ስራቸውን የበለጠ አስፍተው ለመስራት በማሰብ 2010 ዓ.ም 12 በላይ የቤተሰብ አባላትን በመያዝየሀዋሳ ውበት ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ህብረት ስራ ማህበር" በሚል ማህበር መሰረቱ። በሂደትም ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር ህይወታቸውን ከመለወጥ አልፈው ለብዙዎች የስራ ዕድል መፍጠር ቻሉ።

አሁን ላይ ስራው ሰፍቶ በከተማዋ ታዋቂ ሆነዋል፤  የሀዋሳን ከተማ ቆሻሻ 35 በመቶ ይሰበስባሉ፡፡   በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ አካባቢን ማጽዳትን ከሚወገደው ቆሻሻ ደግሞ ገንዘብ ማግኘትን  የዕለት ተግባራቸው አድርገዋል።  ከየአካባቢው በወጣቶች የሚሰበሰበውን ቆሻሻ ገንዘብ ከፍለው በመረከብ አይረባም ተብሎ በተጣለ ቆሻሻ ሀብት ማካበት ተክነውበታል። ወደ ስራ ቦታቸው ጎራ ያለ ሰው ቆሻሻን ያመጡ ደንበኞቻቸው በሰልፍ ገንዘብ ሲቀበሉ ማየት የተለመደ ነው ፡፡

''ቆሻሻ ለእኛ ሀብት ነው፤ የሚጣል ወይም የማይጠቅም የምንለው ቆሻሻ የለም' የሚሉት አቶ ሄኖክ አሁን ላይ  የመኖሪያ ቤት፣የቤት መኪና፣አምስት ቆሻሻ ማንሻ ተሽከርካሪን ጨምሮ ሌሎች ሀብቶችን ማፍራት  ችለዋል፡፡  ማህበሩ በቀጥታ 100 ለሚበልጡ ሰራተኞች ቋሚ የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ቆሻሻን ከተለያዩ አከባቢዎች በማሰባሰብ ወደ ማህበሩ የሚያቀርቡ የበርካታ ዜጎች የገቢ ምንጭ  መሆኑንም ይናገራሉ ፡፡

በቀጣይም ፕላስቲክን የሚተኩ ምርቶች በማምረት በሀገሪቱ በማይበሰብስ ቆሻሻ ሳቢያ የሚፈጠረውን ችግር በአግባቡ ለመከላከል የበኩላችንን ለማበርከት እንሰራለን ሲሉም ይገልጻሉ። በሀገራችን በድግስና ለቅሶ ጨምሮ የፕላስቲክ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን በዚያው ልክ በአግባቡ መሰብሰብና ማስወገድ እንዲሁም መልሶ ለጥቅም እንዲውል የማድረግ ባህል ስለለሌን ለከፋ ችግር እየተዳረግን ነው ያሉት አቶ ሄኖክ ማህበሩ ይህን ችግር ለማስቀረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል

ለዚህ መፍትሄ እንዲሆን በአሁኑ ሰዓት ከሀዋሳ ውጪ 24 አጎራባች ከተሞች ፕላስቲክና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን የሚሰበስቡ ወኪሎች በማስቀመጥ ከከተሞች ጋር በትብብር እንዲሰበሰብ በማድረግ እንደሚቀበሉም አመልክተዋል፡፡ የሚበሰብሰውን ቆሻሻ ወደተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመቀየር ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ገልጸው በዘንድሮ ዓመት ብቻ ወደ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከቆሻሻ በተቀየረ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት ሽያጭ ማግኘታቸውን አመልክዋል፡፡

በስራቸው ትልቁ ተግዳሮትና ችግር ሆኖ የቀጠለው በማህበረሰቡ ውስጥ ቆሻሻን ለይቶ ያለማስቀመጥ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንዛቤ እያደገ የመጣ ቢሆንም ብዙ ሊሰራ ይገባል ብለዋል እንደ ሀገር የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የተነሳ ለውጦች መታየት የጀመሩ ቢሆንም የታሰበውን ግብ እንዲመታ ማህበረሰቡ ቆሻሻን ለይቶ በማስቀመጥና በተገቢው መንገድ በማከማቸት በቆሻሻ ስራ ለተሰማሩ ሰዎች ስራን ማቅለል ብቻ ሳይሆን አካባቢን ከቆሻሻ የጸዳ የማድረግ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ።

ቆሻሻን የመሰብሰብ ስራ ስንጀር በማህበረሰቡ ውስጥ ባለው አመለካከት የተነሳ እስከ መገለልና መሰል ጉዳቶች ቢደርሱብንም ጸንተን በመግፋታችን ዛሬ ኑሯችንን ከመቀየር አልፈን በርካቶች ህይወታቸውን እንዲቀይሩ ዕድል ፈጥረናል የሚሉት ደግሞ የማህበሩ የሒሳብ ክፍል ሰራተኛና የአቶ ሄኖክ ዶንጋቶ ባለቤት ወይዘሮ መሰረት ድጋሎ ናቸው፡፡

ማህበሩ ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘ ሀብት መሆኑን በተጨባጭ እያሳየ ነውያሉት ደግሞ የማህበሩ ጀኔራል ማናጀር አቶ አልታዬ ዬቦ ናቸው።  ይህን ስራ ባለፉት ዓመታት በማከናወን ገቢ ከማግኘት ባለፈ ሀገራዊ የጽዳት ስራ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማና ሌሎች ወኪሎች ባሉባቸው ከተሞች ከግለሰቦች መኖሪያ፣ ከሆቴሎች ከተለያዩ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ቆሻሻ በመሰብሰብና በመለየት የሚመጣውን ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት ቀሪውን ደግሞ መልሶ ለመጠቀም እንልካለን፤  በሂደቱም ፕላስቲክ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከመከላከል ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየተፈጠረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ቆሻሻን ሰብስቦ ወደ ሀብትነት ለመቀየር በሚደረግ ስራ ትልቁ ተግዳሮት ቆሻሻን ለይቶ የማስቀመጥ ባህል ያለማደጉ ነው ያሉት አቶ አልታዬ በዚህ ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተማር ስራ በባለድርሻዎች ሊተኮር ይገባል ሲሉ አመልክተዋል ።ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ምንጭ ቢሆንም ብዙ ዜጎች ያልተሰማሩበትና ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን አንስተው በተለይም ወጣቶች ስራ የለም ከሚል አስተሳሰብ በመላቀቅ  በማህበር በመደራጀት በየአከባቢያቸው ያለውን ቆሻሻ በመሰብሰብ  ወደ ስራ ቢገቡ ለመቀበልና ልምድ ለማካፈል ዝግጁ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

በማህበሩ በቆሻሻ መዛኝነት የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት አቶ አዲሱ ኩኬ ከመንግስት ስራ በጡረታ ከተገለሉ ከዛሬ ሁለት ዓመት ጀምሮ በማህበሩ በመቀጠር ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ የሚደጉሙበት ዕድል እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቆሻሻ ሰብሰባ ስራ ያልተለመደ ቢሆንም ማህበሩ በፈጠረው በጎ ተጽዕኖ በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል

በሲዳማ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ቲቦ በክልሉ ከፕላስቲክ ብክለት የጸዳ አከባቢን ለመፍጠር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ በተለይም የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን ስኬታማ ለማድረግ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል አሰራር ላይ ትኩረት መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ቆሻሻን ወደ ሀብት በመቀየር ህይወታቸውን በማሻሻል ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ከእነዚህም አንዱየሀዋሳ ውበት ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ህብረት ስራ ማህበር"  ለአብነት ጠቅሰዋል።

ማህበሩ የሀዋሳ ከተማን ውብና ጽዱ በተለይም ከፕላስቲክ ቆሻሻ ጽዱ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራትን በእጅጉ እያገዘ እንደሚገኝ ጠቁመው የከተማዋን ቆሻሻ በስፋት በመረከብና ሰብሳቢዎችን በየአከባቢው በማስቀመጥ የመሰብሰብ ስራ እያገዘ ይገኛል ብለዋል

በተጨማሪም በሲዳማ ክልል የሚገኙና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ከተሞች ቆሻሻን በመሰብሰብ ወደ ሀብትነት በመቀየር ለብዙዎች ምሳሌ መሆኑን አመልክተዋል::

ማህበሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የበለጠ እንዲበረታቱ ባለስልጣኑ የህይወት ክህሎት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ጨምሮ የገንዘብና የቦታ አቅርቦት በማመቻቸት የማገዝና የመደገፍ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል:: በተለይም የጽዱ ኢትዮጵያ ዕሳቤን የበለጠ ማስፋት ጠቃሚ በመሆኑ ማህበራትን የማጠናከር ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም