ቀጥታ፡

የአባይ የቁጭትና የወቀሳ ጊዜ አበቃ!  

       የአባይ የቁጭትና የወቀሳ ጊዜ አበቃ!     

(በቀደሰ ተክሌ - ከሚዛን አማን)

አኩርፎ ከቤት ቢወጣ ለመመለስ ሸምጋይ አጥቶ በሰው ሀገር ተንከራታች ልጓም አልባ ሆኖ የኖረው አባይ ከኢትዮጵያ አፈር፣ ማእድናትና ሌሎችንም ሃብቶች ጠርጎ በመውሰድ ለዘመናት ሲፈስ ኖሯል።

ከኢትዮጵያ እምብርት በመነሳት አገራትን አቆራርጦ የሚያልፈው፣ የዓለማችን ታላቁ ወንዝ አባይ በጋና ክረምት ሳይል በመፍሰስ የብዙዎች የህይወት ምንጭ ሆኖ አሁንም ፍሰቱን ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ልጅ የኢትዮጵያውያን አብሮነት ምሰሦ - የወንዞች ንጉሥ ታላቁ አባይ! አሁን ልጓም ተበጅቶለት በፍትሃዊነት ሁሉንም ለመጥቀም ተዘጋጅቶ የማይነጥፈው ጅረት ዘላለማዊ የመፍሰስ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያውያን አመሉ ለከፋ፤ እሺ በጀ አልል ብሎ በእንቢታ ልቡን ባጸና ልጅ አብዝተው ያዝናሉ። የሀዘናቸው ጥግም በሕይወት ሳለ የሞተ ያክል በእንጉርጉሮ ሙሾ ያወርዱለታል። አባይም ይህ እጣ ፈንታ ገጥሞት "አመፀኛ ውሃ" ተብሎ በወቀሳ ተዚሞለታል።

ለኢትዮጵያ ለዘመናት ሳይታዘዝ የኖረው አባይ የአዛዥ እጦት እንጂ በእምቢታ አልነበረም። በዚህ ውጣ በዚህ ግባ ባይ አጥቶ ቦዘነ። በዚህም ተራራውን እየሸሸ ቁልቁል እየተምዘገዘገ፣ ሲሻ እየጬሰ ቁልቁል ወርዶ ከዐለት ጋር እየተጋጨ መዳረሻውንና ማደሪያውን ይናፍቃል። በዚህም ቤቱን ረሳ። ወላጆቹን ትቶ ባእዳንን ብቻ ጦረ፣ ፊቱን በፍጹም ወደ ኋላ እንዳይመልስ እንደ ሎጥና ቤተሰቦቹ ተገዘተ።  

አባይ የባእዳንን ግዝት ከተፈጥሮ ጋር አስተባብሮ በመጠበቅ ሀገሩን ለቆ ከመውጣት ውጭ ቢደክመው የማረፍ፥ ቢመቸው የማልማት መብት ሊያገኝ አልቻለም። ይህ በኢትዮጵያ ልብ ውስጥ ቁጭት ፈጥሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋገረ። 

ኢትዮጵያ ለታላቅ ልጇ ማረፊያ ሠርታ ጎጆ ልታወጣ ቋመጠች። ፈተናው በዛ የፖለቲካ መልክ ይዞም አቅሟን ተፈታተነ። ስደተኛው አባይን ስላሳረፉት እርሱም ስለመገባቸው የግል ሀብት አድርገው የቆጠሩት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጫና ፈጥረው የሀሳብ ጽንሱን ከታሪካዊና ቀጣናዊ ጠላቶች ጋር እየተባበሩ አቋረጡት።

አባይን ገድቦ የመጠቀም የዘመናቱ የኢትዮጵያ መሪዎች ጉጉቱ ህልም ሆኖ ሐዘኑ ከነ ቁጭቱ ቀጠለ። እንጉርጉሮ ወቀሳ በበዛባቸው ስንኞች ቋጥሮ መዜሙን ቀጠለ። የኢትዮጵያ ዐይኖች ጀግንነት በአባይ ሲሸበብ ማየት አንገሸገሻቸው። የበይ ተመልካች መሆንና ከጓሯቸው ሞፈር አስቆርጦ መራብ አመማቸው። 

ኢትዮጵያዊነት ከዘመን ዘመን የማይነጥፍ፥ ልብ ለልብ የተሳሰረ ትውልድ ማንነት ማሳያ ሐውልት ነው። ትላንት ዛሬን እያቃና ነገን የሚገነባበት ሀገራዊ ራእይ ያላቸው መሪዎች ትስስር በአባይ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል። 

ከ1929 እስከ 1950ቹ ያለው የአባይ ፖለቲካ ጉዳይ በብዙ ድርድሮችና ስምምነቶች ታጀበ። የጫና ፈተናው አየለና ገንብቶ የመጠቀም ጥንስስን ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር አደረገ። ያኔ ነገን የተመለከተ ዐይን  "ልጆቻችን ይሠሩታል" የሚል ቃል ሰጠና ኢትዮጵያ ልጆቿን በተስፋ ተጠባበቀች።

ዘመን አለፈ ትውልድ ተተካ ልጆችም ተወለዱና የተስፋ ቀጠሮ ደረሰ ወርሃ መጋቢት 2003 ዓ/ም። በዚህ ቀን የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዜና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተበሰረ። ኢትዮጵያ እልል አለች፤ "እንጉርጉሮ ይብቃ" ተባለ በዜማ በዝማሬ አባይ ተሞገሰ። የአባይ የወቀሳ ጊዜ ተጠናቀቀ- የቁጭት ጊዜ አብቅቶ የስኬትና ማንሰራራት ጊዜ መጣ። ለግድቡ የ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት ከአንድ ብር ጀምሮ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ በእውቀትና በጉልበት የተጉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የደስታ ቀንም እውን ሆነ።

በጉባ ሰማይ ስር አዲስ ክስተት፣ አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ስም ተተከለ። አባይ ከሚል ነጠላ ስም ወደ "ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ" ተሻገረ። የድግቡ ሃይቅም "ንጋት" የሚል መጠሪያ ወጥቶለት ለኢትዮጵያ የንጋት ጸሃይ እየወጣች መሆኑን ለሁላችንም ብስራት ሆነ።

"እንኳንም ጀመርን፣ እንኳንም በር ተከተፈተልን" እንጂ ያሉት ልበ ኩሩና ክንደ ብርቱ ኢትዮጵያውያን ጫናዎችን በአይበገሬነት መንፈስ ድባቅ እየመቱ ጉዞ ወደ ፊት ቀጠሉ። ወደ ተግባር ገብተው "ሕይወታችንንም ቢሆን ለአባይ አንሰስትም" አሉ። 

ግድቡን እንሠራለን ብለው የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከነ አባባላቸው "የነብር ጭራን አይያዙ፥ ከያዙም አይለቁ" ነውና ሥራውን ስለጀመሩት የአባይ ግድብ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳቸውና ደም ስራቸው ሆኖ ቀጠለ። እንደ ዐይን ብሌናቸው ያዩ፣ ይጠብቁት እና ይሳሱለት ጀመር። 

የአልሸነፍ ባይነት ወኔን ከጀግንነት ጋር አጣምረው የያዙ ኢትዮጵያውያን የጠላት ነቀፋና ፕሮጀክቱን የማኮላሸት ሴራን እንደ ድር አብረው ተከላከሉ። የ"እንችላለን" ትርክትን በተግባር ነፍስ እየዘሩ እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ከሕዳሴ ጋር ቀጠሉ። በጉባ ምድር ላይ የአንድነታቸውን ቋሚ ሐውልትም ተከሉ። 

ኢትዮጵያውን ከአድዋ ጦርነት ወዲህ የአንድ ቃል ተናጋሪ የአንድ ልብ መካሪ ሆነው የተከሰቱበትና በአንድ የተመሙበት ትልቁ የታሪክ አሻራ አባይ በሕዳሴ ሆነ። የተማሪ ቦርሳ፣ የእናቶች መቀነት፣ የአረጋውያን የጡረታ ደብተር፣ የአርሶ አደሮች ጎተራ፣ የአርብቶ አደሮች በረት፣ የመንግሥት ሠራተኛው ፔሮል፣ የነጋዴው ኪስ እና የዳያስፖራ ዋሌት ሳይቀር በአባይ ላይ አሻራ አለው። 

የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ኢትዮጵያ ራሷን በዓለም መድረክ ከፍ አድርጋ ያሳየችበት ትልቅ  አጋጣሚ ነው። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደረሰውን ውሃ አይሞላ ክስ በብስለት መክታ እውነትን ለዓለም ሕዝብ አስገንዝባለች። በዚህም የዓለም አቀፍ ሕግ አዋቂነቷንና አክባሪነቷን፣ የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎቷንና ለሰላም ያላትን አቋም ቁልጭ አድርጋ አረጋግጣለች። ድርድሮችን በድል የሚቋጩ ልጆቿ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ዘርፍ ብቁ የመሆናቸው ነጸብራቅ ሆነው ተከሰቱ።  

ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ሥራው ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እስከ ጉምቱ አምባሳደሮች በተናበበ መልኩ ብቅ ብሎ አጀብ አስብሏል።  ድርድሩ በመስመሩ፣ የዲፕሎማሲ ሥራው በሜዳው ፖለቲካ እና ሌላው የሀገር ጉዳይ በየፈርጁ እየቀጠለ የሕዳሴው ግድብም ለደቂቃ እንኳ ሳይቆም ይሠራ ነበር። ይህ የመብቃት፣ የማደግ፣ በጥበብ የመበልጸግ፣ በሀሳብና አቅም የመብሰል ሀገራዊ ማሳያ ነው። ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን አሻጋሪ የተግባር ልምምድ መሆኑም አያሻማም። ለዚህ ግድብ ስኬት ደግሞ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን መሪ ሆነው ብቅ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶር) ማንሳት ግድ ይላል።

አዛዥ አጥቶ ቦዝኖ የነበረውን ጊዜ ለመካስ ና ብሎ የሚጣራውን አዛዥ "አቤት" ብሎ ትዕዛዝ ለመቀበል አባይ አላቅማማም። አሁን በሙሉ ልቡ ወደ ጫጉላ ቤቱ ገብቷል። የመስከረሙ ሙሽራ የቤት ሀብት ዘርፎ ለባዕድ አሳልፎ ከመስጠት ተቆጠበ። የበረሃው ሀሩር ሳይመታው በሀገሩ እፎይ ብሎ ብርሃንም ምግብም፣ ሀብትም ክብርም መሆን ጀመረና የኢትዮጵያን ክብር ዳግም ከፍ አደረገ።

ሰው ተፈጥሮን ሲያዝ እሺ ይላል፥ ዝም ካሉት በራሱ ፍላጎት ይሔዳል። ይህ ተፈጥሯዊ የአባይ ግብር ተቀይሮ በሰዎች መታዘዝ ጀመረ። አፈርና ውሃ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የብርሃን ምንጭ ሆኖ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብርሃን መሆን ጀምሯል። 

በሕዳሴ ግድብ ታዞ ፊቱን ወደ ልማት ሥራ ያዞረው አባይ ያለፈውን ለመካስ ብዙ ጸጋዎችን ይዞ ተከሰቷል። የዓሳ ምርት፣ ግዙፍ ሀይቅ ከደሴቶች ጋር አንጣሎ በመያዝ የኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ መሪ ሊሆን ቆርጦ ተነስቷል። 

አብሮ የመልማት የኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት በወለደው እሳቤ ህዳሴ ግድብ የጎረቤት አገራት ሃብት ጭምር በመሆን ለማገልገል ተዘጋጅቷል።

አባይ ሆይ ስምህ ከወቀሳ ወጥቶ በሙገሳ ስለተተካ እንኳን ደስ አለህ!

እናቴ ሆይ የተፈታው መቀነትሽ ሀይል ስላመነጨ ለልጆችሽ ሀብት አውርሰሻልና ደስ ይበልሽ።

ሀገሬ የብርሃን ዘመን ስለፈነጠቀብሽ እንኳን ደስ አለሽ!

ሰላምና ፍቅር ለሁላችን ይሁን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም