የትውልዱ ድል፤ የብርሃን ጅረት - ኢዜአ አማርኛ
የትውልዱ ድል፤ የብርሃን ጅረት

አቶ ዲሮ ቱፋና ዓለሚ በዳዳ በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልምራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው።
አካባቢያቸው ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ ቢሆንም እስካሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ያነሳሉ።
የኤሌክትሪክ ሃይል ሽፋን ባለመዳረሱ ምክንያት ኑሯቸው አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፤ ማገዶ መጠቀማቸው ደግሞ ለጤናቸው ተግዳሮት እየሆነባቸው መጥቷል።
እነርሱ እንደሚሉት የማገዶ እንጨት ለማምጣት ረጅም ርቀት በመጓዝ ለእንግልት ተዳርገዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዋ አበበች ደጎሽም በአካባቢያቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት ሕይወታቸውን ፈታኝ አድርጎታል።
ልጃቸው ለማጥናት የሻማና ኩራዝ መብራት ለመጠቀም ትገደዳለች።
በዚህ ላይ ምግብ ለማብሰል ከሰል መጠቀማቸው በጤናቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መጥቷል፤ በተለይ በመተንፈሻ አካላቸው ላይ ያጋጠማቸው እክል ለሀሳብ ዳርጓቸዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞንና በቤንች ሸኮ ዞን ያሉት ሁለቱን ቤተሰቦች ተስፋ ያስተሳስራቸዋል።
ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎታቸው ምላሽ ለማግኘት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚመነጨውን ሃይል በተስፋ ይጠባበቃሉ።
በመላው ኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት፣ የገንዘብ መዋጮና የተቀናጀ ትብብር እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይዞ እየመጣ ካለው የ5 ሺ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ተቋዳሽ እንደሚሆኑ ይተማመናሉ።
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረተ ድንጋይ በቤንሻንጉል ጉምዝ ጉባ ወረዳ ከተቀመጠ ከዓመታት በኋላ መጠናቀቁን ተከትሎ እንደ አቶ ዲሮ ቱፋና ዓለሚ በዳዳ ያሉ ተስፋቸው ለምልሟል።
ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ተቋድሰው መብራት በማግኘት ኑሯቸውን የሚያሻሻሉበትን መንገድ በተስፋ ይጠባበቃሉ።
ለዚህም ነው ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን በዓባይ ወንዝ ላይ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማዋጣት የግድቡን ግንባታ በቁርጠኝነት ያካሄዱት።
መነሻውን ከኢትዮጵያ አድርጎ 6 ሺ 696 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚጓዘው የዓባይ ወንዝ ከዓለማችን ረጃጅም ወንዞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው።
ረጅም ኪሎ ሜትር ለሚጓዘው የዓባይ ወንዝ 86 በመቶ የውሃ ድርሻ የምትሸፍነው ደግሞ ኢትዮጵያ ናት።
ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለአቶ ዲሮና መሰሎቻቸው ኑሯቸውን ለማቃለል የሚያስችል የመብራት ሃይል ከማቅረብ ባሻገር ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል በመሸጥ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል አቅም እንደሚሆን ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።
ይህ ደግሞ የተፋሰሱ አገሮች በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት መተሳሰር የሚያስችል፣ በጋራ በመልማት ዕድገታቸውን ለማፋጠን እድል የሚከፍት መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚስማሙት።
ይህ ግን በቀላሉ የተገኘ ዕድል ላለመሆኑ ያለፉት ዓመታት ተግዳሮቶች ተጠቃሽ መሆናቸው አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
የቀድሞው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ቡድን አባልና የውሃ ሃብት አስተዳደር፣ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጓተት፣ መንግስትና ህዝብ ተስፋ ቆርጠው እንዲተውት ብዙ ሙከራዎች ቢደረጉም በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ማጠናቀቅ መቻሉን ያነሳሉ።
የዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ባለሙያው ከበደ ገርባ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ከዓባይ ውሃ ለመነጠል ዘርፈ ብዙ አደናቃፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ቢሰሩም ግንባታውን ማስተጓጎል ያለመቻሉን ነው አጽንኦት የሰጡት።
የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ግንባታው እንዳይጠናቀቅ ከውጭ ሃይሎች ባለፈ በአገር ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር መግለጻቸውን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል።
በኢትዮጵያ ለውጥ ከመጣ በኋላ መንግስት ግድቡ ላይ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ተገንብቶ እንዲያልቅና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መስራቱ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የተፋሰሱ አገሮች የዓባይ ወንዝን በፍትሃዊነት የመጠቀም አስፈላጊነትን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጀመር በተግባር የተገለጠ እርምጃ መውሰዷ በአካባቢው አገሮች ላይ ተስፋን አጭሯል።
ለዚህም ነው የናይል ተፋሰስ አገራት በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም እሳቤ እንዲኖራቸው የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሰነድ (CFA) እ.አ.አ በ2010 ተዘጋጅቶ አገሮች እንዲስማሙ እድል የተሰጠው።
ይህም ለዓባይ ውሃ ምንም ድርሻ የሌላቸው የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 የዓባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም የተፈረሙትን የቅኝ ግዛት ውሎች ውድቅ የሚያደርግና በተፋሰሱ አገራት መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።
የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሰነድ እ.አ.አ በ2010 ለፊርማ ክፍት ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ብሩንዲ ፈርመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውሃ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ኤርሚያስ ተፈሪ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የማዕቀፍ ስምምነቱን ስድስቱ አገራት ሰነዱን በፓርላማቸው ካጸደቁ የናይል ኮሚሽን ማቋቋም ይችላሉ።
እንደ ቀድሞው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ቡድን አባልና የውሃ ሃብት አስተዳደር ፣ወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና የሃይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ፤ በአሁን ወቅት ስድስቱ አገራት ስምምነቱን መፈረማቸውን ተከትሎ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ተቋቁሟል።
የውሃ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ኤርሚያስ ተፈሪ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ከዓባይ ተፋሰስ አገራት መካከል ግብጽና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል ሽፋናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ሊነጻጸር የማይችል መሆኑን ነው የሚያነሱት።
ይህም በጤና፣ በትምህርት እና በኑሮ ዘይቤ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ይህን ችግር ለማቃለልና ብርሃንን ለሁሉም ለማዳረስ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግድ ይላሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በ''እንችላለን'' መንፈስ ከተማሪ እስከ ሰራተኛ፣ ከጡረተኛ እስከ ወታደር፣ ከቤት እመቤት እስከ ባለሃብት ሁሉም በደረጃውና በአቅሙ በገንዘብ በሀሳብና በጉልበት ለመሳተፍ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግ ተረባርበዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራስ አቅም በራስ ዕውቀትና ሀብት የማይቻል የሚመስለውን ችለው ያሳዩበት አኩሪ ታሪክ ነው ይላሉ።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መጻዒ ዕድሉን የተሻለ ለማድረግ ከዕውቀቱ፣ ከገንዘቡና ከጉልበቱ አዋጥቶ እውን ያደረገው የዳግማዊ ዓድዋ ድል መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ናቸው።
የዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ባለሙያው ከበደ ገርባ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ መጠናቀቁ የትውልዱ ድል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ሥነ-ሥርዓት ላይ በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል ፣ታሪክ መስራት ደግሞ ድል ነው ይላሉ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የአሁኑ ትውልድ ዕድልና ድል መሆኑንም ነው ያነሱት።