የኢትዮጵያ የካርቦን ገበያ፤ፍትሃዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦት ማግኛ አማራጭ --- - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የካርቦን ገበያ፤ፍትሃዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦት ማግኛ አማራጭ ---

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
“ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፤ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።
ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ የካርቦን ሽያጭ ይገኝበታል።
የካርቦን ንግድ ማለት የካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትሉ ጋዞችን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚደረግ የገበያ ዘዴ ነው። ልክ እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ የካርቦን ልቀትን የመገበያያ ዕቃ አድርጎ ይቆጥረዋል።
መንግስታት ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኩባንያዎች ወይም ተቋማት ሊለቁት የሚችሉትን ከፍተኛውን የካርቦን መጠን ይወስናሉ።ይህ መጠን “የልቀት ጣሪያ” (Emission Cap) ይባላል። ከዚያም እያንዳንዱ ኩባንያ ይህን ያህል ካርቦን የመልቀቅ “ፈቃድ” ወይም “ክሬዲት” (Credit) ይሰጠዋል።
ካርቦን ክሬዲት፦ ኩባንያዎች እንደ ደን ልማት ወይም የታዳሽ ኃይልን በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ብድር የሚያገኙበት ስርአት ነው።
የካርቦን ንግድ ሀገራት፣ኩባንያዎች እና ግለሰቦች በተገዢነት እና በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚያከናወኑት ነው።
አፍሪካ በዓለም ደረጃ ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቀው በካይ ጋዝ ልህቀት ከአራት በመቶ ያነሰ ድርሻ ቢኖራትም የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ዳፋ ተሸካሚ አህጉር ሆናለች።
የካርቦን ገበያ ለአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ለስራ እድል እና ለብሄራዊ አየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች ትግበራ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የአፍሪካ ሀገራት በ2015 ዓ.ም በግብጽ ሻርም አል ሼክ በተካሄደው 27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንበረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-27) የአፍሪካ ካርቦን ገበያ ኢኒሼቲቭ ይፋ አድርገዋል።
በኢኒሼቲቩ አማካኝነት አፍሪካ በዓመቱ በ300 ሚሊዮን የካርቦን ክሬዲት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች። እ.አ.አ በ2030 በካርቦን ንግድ ለ30 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ውጥን ተይዟል።
የካርቦን ገበያ በአፍሪካ ሀገራት ተስፋ ሰጪ እድገት እያሳየ ይገኛል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ እና ሴኔጋል የካርቦን ገበያ የአሰራር ማዕቀፎችና ግቦች አዘጋጅተው እየሰሩ ይገኛል።
የአፍሪካ ልማት ባንክም የካርቦን ገበያ የፋይናንስ አማራጭ በማዘጋጀት ሀገራት ማዕቀፎች እንዲቀርጹና የካርቦን ክሬዲት በአፍሪካ የአክሲዮን ገበያዎች ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓል።
የአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) በአህጉሪቷ የካርቦን ገበያ ቀረጻ፣ ትግበራ እና የግብይት ስርዓቱን የሚወስን “African Gold Standard” የተሰኘ የአሰራር ማዕቀፍ አዘጋጅቶ እየተገበረ ይገኛል።
ማዕቀፉ የካርቦን ገበያ ማህበረሰቦች ካርቦንን በማመቅ ስራቸው ተጨባጭ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና ለብዝበዛ እንዳይጋለጡ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት መንገድ ነው።
የአየር ንብረት ጉባኤውን የምታዘጋጀው ኢትዮጵያ በካርበን ገበያ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ቀርጻ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሆነች የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የእርምጃዎቹ አንድ አካል የሆነው የካርቦን ግብይትን በውጤታማነት ለመምራትና ተጠቃሚ ለመሆን ብሔራዊ የካርበን ግብይት ስትራቴጂ አዘጋጅታለች።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የካርቦን ግብይት ስትራቴጂ የመጨረሻ ረቂቅ ግምገማ እና የካርቦን ገበያ የህግ ማዕቀፍ የህግ ክፍተት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት (Validation Worksop on draft Ethiopia’s National Carbon Market Strategy and Consultation on the Legal Gap Analysis Report) ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ አካሄዶ ነበር።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ስትራቴጂውን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት ከስትራቴጂ ዝግጅቱ ጎን ለጎን የካርቦን ገበያ ሊመራበት የሚችል የህግ ማእቀፍ ለማዘጋጀት የህግ ክፍተት የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
የማዕቀፉ ዓላማ በኢትዮጵያ በአግባቡ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል የህግ ማዕቀፉን በፍጥነት አዘጋጅቶ በማጸደቅ የካርቦን ግብይት ላይ በንቃት እና የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የካርቦን ገበያ ልማት ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ እና የካርቦን ገበያ ንግድ የህግ ማዕቀፍ ዳሰሳ ጥናት ሰነድ ግብአቶችን አካቶ በማዳበር ያሉትን ሂደቶች በማለፍ በቅርብ ጊዜ ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ መዘጋጀቱ ኢትዮጵያ በደን ልማት፣በትራንስፖርት፣ በቆሻሻ አወጋገድና በኃይል አማራጭ ልማት ላይ በምታበረክተው ልክ ተጠቃሚ የሚያደርጋት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በዚህም ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በማሳለጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራን ለማገዝ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ከኖርዌይ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም የተፈራረመችው የ75 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የካርቦን ሽያጭ ስምምነት በካርቦን ግብይቱ እያገኘች ያለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሳይ ነው።
እ.አ.አ እስከ 2026 ድረስ የሚቆየው ስምምነት ከካርበን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ እንደ ሀገር የተሰሩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የደን ልማት ስራዎችን ለመስራት ይውላል።
በባሌና ምዕራብ አርሲ ጥብቅ ደኖች ሲተገበር በቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ) አማካኝነት እየተከናወነ ያለው የካርቦን ንግድ በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር ብር ገቢ እየተገኘበት ነው።
ፕሮጀክቱ በመተግበሩ ጉዳት ይደርስበት የነበረው የደን ሀብት መጠበቅ እና የካርቦን ጋዝ ልቀትን ማስቀረት ተችሏል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የካርቦን ገበያ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ በሀገሪቷ የተለያዩ ጥብቅ ደኖች ካርቦኖችን በማከማቸት ገቢ እንዲገኝ እየሰራች ነው።
የካርቦን ግብይት የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ የማግኘት አማራጭ በማስፋት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት እና የካርቦን ገበያ የአሰራር ማዕቀፍ በመዘርጋት እያከናወነች ያለው ስራ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው።
በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም በካርቦን ገበያ ያላትን ተሞክሮ ታቃርባለች ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው ላይ የካርቦን ገበያ የበካይ ሀገራት እና ኩባንያዎች የገንዘብ መክፈያ ዘዴነት ወጥቶ በአፍሪካውያን ባለቤትነት እንዲመራ መሪዎች ጠንካራ ጥሪ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
አፍሪካ በጉባኤው ላይ ጠንካራ የካርቦን ገበያ አስተዳደር ስርዓት መገንባት፣የካርቦን ክሬዲት ሽያጭ ላይ የሚያጋጥሙ የክፍያ ክፍተቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የበለጠ ማረጋገጥ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እና ፍትሃዊ ገቢ ማግኘት ላይ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የካርቦን ገበያ በተገቢው ሁኔታ የሚፈጸም እና የአፍሪካን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ከሆነ ለአህጉሪቷ ዘላቂ የፋይናንስ አማራጭ፣ አይበገሬነትን ለመገንባት እና ዘላቂ እድገትን ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።