በደን ውስጥ ያረፈ አረንጓዴ አሻራ ምግብ እና ገንዘብ የሆነባት - ቤንች ሸኮ ዞን! - ኢዜአ አማርኛ
በደን ውስጥ ያረፈ አረንጓዴ አሻራ ምግብ እና ገንዘብ የሆነባት - ቤንች ሸኮ ዞን!

(በቀደሰ ተክሌ)
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኘው የቤንች ሸኮ ዞን አረንጓዴና የምድር ገነት ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ነው።
ይህ አካባቢ በተፈጥሮ የተቸረው ሰፊ የደን ሽፋን ያለው ሲሆን ደኑ ክብሩን ጠብቆ ከዘመን ዘመን የመሸጋገሩ ምሥጢር ደግሞ በአካባቢው ብሔረሰቦች ዛፍ መቁረጥን እንደ ነውር የማየት ባህል መሆኑ ነው።
በአካባቢው ዛፍ መቁረጥ ነውር ነው። ደፍሮ ያለአግባብ ቆርጦ ዛፍን ከቦታው የሚያጠፋ በአካባቢው ሽማግሌዎች ይረገማል።
በዞኑ ዛፍን ቀርቶ ከዛፉ ጋር ተያይዞ የወጣን ሐረግ እንኳ በዘፈቀደ መቁረጥ አይፈቀድም። ለቤት መሥሪያና ሌሎች አገልግሎቶች ለመጠቀም ሲፈለግ እንኳን ጥቅጥቅ ያለ ደን እንዳይሳሳ አለፍ አለፍ ብሎ በጥንቃቄ የመቁረጥ ተሞክሮ አላቸው።
ለቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች በቤታቸው ቅርበት ላይ ዛፍ መትከል ቅንጦት ሳይሆን እንደ መሠረታዊ የኑሮ ዘዬ ተደርጎ ይቆጠራል።
በአረንጓዴ ልምላሜ ያልተከበበ ቤት የሰነፍ ቤት ነው። ከዛፎቹ አንዱ ቢቆርጥ እንኳ ሌላ ከስር ይተካል እንጂ እንዲሁ አይተውም።
የአካባቢውን ልምላሜና አረንጓዴ ገጽታን ጠብቆ ያቆየው ይህ ባህል የቤንች ሸኮዎች ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የሚጠቀሙበት በጎ እሴታቸው ነው። በፍቅር የሚማግ ንጹህ አየር እና ኩልል ያሉ ምንጮች፣ ፏፏቴዎችና ክረምት ከበጋ የማይደርቁ ወንዞች ሕያው ምስክርና ሌላው የአካባቢው ድምቀቶች ናቸው።
የቤንች ሸኮ ዞን ለምለም የተፈጥሮ ደን፤ ደን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ምንጭም ጭምር ነው። መኖሪያ ቤቶችን የከበቡ ዛፎች የማንጎ፣ የብርቱካን፣ የፓፓያ፣ የአቮካዶ፣ የሙዝ፣ የእንሰት አሊያም ሌላ ለምግብነት የሚውሉ ናቸው።
እምቅ የሆነው የተፈጥሮ ደን ደግሞ በውስጡ ቡና፣ ኮረሪማ፣ ጥምዝ እና ሌሎችንም ቅመማ ቅመሞችን ያቀፈ ነው። ይህ እምቅ የኢኮኖሚ አቅም ለአካባቢው ማኅበረሰብ አለኝታም ሆኑ እያገለገለ ይገኛል። ለዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ብዙ ጊዜ "ደን ሕይወታችን ነው" ሲሉ ይደመጣሉ። አዎ ደን ሕይወት ነው፣ ደን እስትንፋስ ነው፣ ደን ምግብና ውሃም ጭምር ነው።
ትናንት የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከናወነበት የሸኮ ወረዳ "አሞራ ገደል" የተባለ ድንቅ ተፈጥሯዊ ገጽታ አለው።
አሞራ ገደል ጥቅጥቅ ባሉ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ከመከበቡ ባሻገር ከስር ወንዝ እያለፈ ከላይ ተሽከርካሪ የሚያልፍበትን በተለምዶ "የእግዜር ድልድይ" እየተባለ የሚጠራውን ግዙፍ ድልድይንም በውስጡ ይዟል።
አረንጓዴ ካባ የደረበው ጋራ ሸንተረሩ ለዓይን የሚማርክ መስህብ ስፍራም ጭምር ነው። የደኑ ጫፍ ከ20 የሚበልጡ ፍል ውሃዎችን በአንድ ሰብስቦ በመያዙ በየእለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከደዌያቸው ለመፈወስ ሲሉ ወደስፍራው ይመጣሉ።
ታዲያ በዚህ ደን ተከበው የሚኖሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ችግኝ ከመትከል አልቦዘኑም። ባላቸው ከመኩራራት ይልቅ ትርጉም ባለው መልኩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ ነው። ዛሬም በትጋት ችግኝ እየተከሉ ነው፤ ነገም ይቀጥላሉ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከፍራፍሬ ባሻገር የነገን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሰብ የቁንዶ በርበሬ ቅመም ለማልማት በማቀድ የግራቪላ ዛፍ ተከላ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው።
ይህ እሳቤ ደን ውስጥ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ችግኝ እንዲተክሉ እያደረጋቸው ነው። በደኑ ዙሪያ ያሉ ገላጣ ሜዳዎች በችግኝ እየተሞሉ ነው።
የአርሶ አደሩ ማሳም በፍራፍሬ ተንበሽብሿል። በተለይ አካባቢው ለፍራፍሬ ምርት ያለው ተስማሚነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ስለሚያደርጋቸው በራሳቸው በቅለው በማደግ ላይ ያሉ የደን ዛፎችን አንስተው በፍራፍሬ ይተካሉ።
ይህ ወቅቱ የሚጠይቀው ብልህነት የተሞላበት የልማት አርበኝነት ነው፤ የአካባቢውን ስነ ምህዳር እየጠበቁ በኢኮኖሚ የመበልጸግ ትልም ያለው ጉዞ ማሳያም ነው።
በዚህም የቤንች ሸኮ ዞን ባለፉት ዓመታት በተተከሉ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ በፍራፍሬ ዘርፍ ሰፊ ውጤት ከተመዘገበባቸው የክልሉ አካባቢዎች የሚጠቀስ ነው።
ለአብነትም በደቡብ ቤንች ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የጃንቹ ተራራ "የአረንጓዴ አሻራ ልማት ያከበረው ተራራ" መሆን ችሏል።
ስፍራው ምንም እንኳ ፍጹም ገላጣ ባይሆንም ለእርሻ ሥራ የማይመች በመሆኑን ለዘመናት ጾሙን አድሯል። የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከተጀመረ ወዲህ ሙሉ በመሉ የሙዝ ችግኝ ተተክሎበት ዛሬ ላይ የሙዝ ፍሬ የሚሰበሰብበት የኢኮኖሚ ማዕከል ሆኗል ማለት ይቻላል።
ይህ ተሞክሮም የበርካቶችን ወኔ ቀስቅሶ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ ላይ በራስ ተነሳሽነት እንዲዘምቱ ምክንያት ሆኗል። ክረምትን ብቻ ሳይጠብቁ የበልግ ወራትንም መደበኛ የችግኝ ተከላ ወቅት አድርገው ቡናን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ችግኞችን አርሶ አደሮቹ በማሳቸው በስፋት ይተክላሉ።
በቤንች ሸኮ ዞን በደን ውስጥ ያረፈ አረንጓዴ አሻራ ዛሬ ምግብ ነው፤ ገንዘብም ነው። የዛሬ ሦስት ዓመት በዚሁ የአረንጓዴ አሻራ ያለሙት የሙዝ ችግኝ ለፍሬ መድረሱን ከተናገሩ አርሶ አደሮች መካከል የሸኮ ወረዳ ነዋሪው ሁሴን እንድሮ ተጠቃሽ ናቸው።
ሙዝ ብቻ ሳይሆን የተከሉት የግራቪላ ችግኞች አድገው ከሥራቸው የተተከለው የቁንዶ በርበሬ ቅመም ተስፋ ሰጪ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአካባቢው የፍራፍሬ ምርት መጨመሩን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ምሳዬ መሐመድ ናቸው።
ዋጋውም የተረጋጋ፣ አቅርቦቱም ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ነው የገለጹት። ይህን መነሻ ሆኗቸው እርሳቸውም ችግኝ በመትከል አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ናቸው።
የቤንች ሸኮ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ እንደሚሉት በዞኑ ችግኝ የሚተከለው ገላጣ ቦታዎችን በመፈለግ ብቻ ሳይሆን ከጥቅጥቅ ደኖች ውጭ ያሉ የባህር ዛፍና ተጨማሪ ጥቅም የሌላቸውን ዛፎች በማንሳት ጭምር ነው።
ለአብነትም የባህር ዛፍ ደንን አንስተው በቦታው የተተከለው ሙዝ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅ ባሻገር ፍሬ በመስጠት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና እያረጋገጠ ነው።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ30 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የማሳ ሽፋኑን ለማሳደግ ታልሞ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አቶ መስፍን እንዳሉት ከአምስት ዓመታት በፊት በዞኑ የነበረው 29 ሺህ ሄክታር የፍራፍሬ ማሳ ዛሬ ላይ ወደ 100 ሺህ ሄክታር ማሳ አድጓል።
ይህም በየቀኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች ከዞኑ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የፍራፍሬ ምርት ጭነው እንዲወጡ እያስቻለ ነው። በዚህም ተጨባጭ ውጤት የአርሶ አደሩ ኑሮ እና የዞኑ ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን አቶ መስፍን ይገልጻሉ።
የቤንች ሸኮዎችን ተሞክሮ ያነሳንበት ዋና ዓላማ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ እና ደን ልማት ያለፈ አንድምታ እንዳለው ለማሳየት ነው።
ደን አለን ብለው በመኩራራት ያልተቀመጡ የቤንች ሸኮ እጆች ዛሬ የልማት ትሩፋታቸውን እየለቀሙ ነው። በመትከል መመገብ፣ በመትከል ሀብትን ማካበት፣ በመትከል ከድኅነት ወደ ራስን መቻል ማንሠራራት እንደሚቻል የእነሱ ልምድ ለብዙዎች ተሞክሮ ይሆናል። ሰላም!