በቤተሰብ የተቀረፀው የእህትማማቾቹ የሃገር ፍቅር ስሜት - ኢዜአ አማርኛ
በቤተሰብ የተቀረፀው የእህትማማቾቹ የሃገር ፍቅር ስሜት

በቤተሰብ የተቀረፀው የእህትማማቾቹ የሃገር ፍቅር ስሜት...
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በገጠሟት ችግሮች ሁሉ የበርካታ ጀግኖች መፍለቂያ መሆኗን ያረጋገጠች ሀገር ናት፤ ይህም በአለም አደባባይ ነጻነቷ ተከብሮ፣ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ምክንያት ሆኗል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች መስዋእትነት ሉአላዊነቷን አስጠብቃ ኖራለች፤ ወደፊትም ነጻነቷ የተከበረ፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ዜጎች ኮርተው የሚኖሩባት ጠንካራ ሀገር ሆና ለመቀጠል በላቀ ትጋት ላይ የምትገኝ ሃገር ናት።
ይህ ጽሁፍ በላቀ የሃገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተው፤ ለግዳጅ ተዘጋጅተው የራሳቸውን የጀግንነት ህልምና ትልም እውን ለማድረግ በብር ሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጥነው በተመረቁ እህትማማቾች ላይ ያተኩራል።
ውልደትና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ የሆኑት እህትማማቾቹ ስመኝ ወርዶፋ እና ቃልኪዳን ወርዶፋ በብር ሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመሰረታዊ ወታደርነት ሰልጥነው ተመርቀዋል።
ከቤተሰባቸው የወረሱት ከፍተኛ የሃገር ፍቅር ከህጻንነታቸው ጀምሮ በልባቸው እየተብላላ፣ በአዕምሯቸው እየተብሰለሰለና መዳረሻውን እየፈለገ መኖሩን አስረግጠው በኩራት ይናገራሉ።
ለሃገር ፍቅር ስሜቱ ምንጭና ጥንስሱም መኖር፣ ማጌጥ፣ መደሰት፣ ማዘን… የሚቻለው በሀገር ላይ ነው፤ ሀገር ስትኖር ሁሉም ህልምና ትልም ይሳካል ተብሎ እየተነገራቸው ማደጋቸው ነው።
እህትማማቾቹ ለዘመናት ህልማቸው የሆነውና በልባቸው እየሰረጸ በውስጣቸው እየታገላቸው የሚገኘውን የሃገር ፍቅር ስሜት እንዴት፣ መቼና የት እውን እንደሚያደርጉት ማሰላሰል ከጀመሩ ከራርመዋል።
ይህንን ህልማቸውን እውን የሚያደርጉበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ እያሉ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ማስታወቂያ ማውጣቱን ተመለከትን ይላሉ።
ይህም የህልምና ትልም ታሪክ በብር ሸለቆ መሰረታዊ ወታደር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመሰልጠን ተመራቂ ሆነው ተገኝተዋል።
መሰረታዊ ወታደር ስመኝ ወርዶፋ ከኢዜአ ጋር በነበራት ቆይታ፤ በራሳችን ሙሉ ፈቃድ ወደዚህ ታላቅ ተቋም መቀላቀላችን እኔም ሆንኩ እህቴ በጣም ደስተኛ ነን ስትል በልበ ሙሉነት ገልጻለች።
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ያወጣውን ማስታወቂያ እንዳየሁ "ለታናሽ እህቴ ቃልኪዳን የዘመናት ህልማችን እውን የምናደርግበት ታላቅ ብስራት ነው ብዬ ነገርኳት" የምትለው ስመኝ፤ በዚህም ውጥናችንን የምንተገብርበትን መንገድ ለመጀመር አላቅማማንም ብላለች።
ምንም እንኳ በልባችን ፀንቶ ከአካላችን ጋር እያደገ የመጣው የላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት ሁለታችንንም ገፋፍቶን በጉዳዩ ላይ መክረን እድሉን መጠቀም እንዳለብን መግባባት ላይ ሊያደርሰን ችሏል ትላለች መሰረታዊ ወታደር ስመኝ።
በፈቃዳችን ተመዝግበን ወደ ብር ሸለቆ በመምጣት የስነ ልቦና፣ የቴክኒክ፣ የአካል ብቃትና የውጊያ ስልቶችን በተግባርና በንድፈ ሃሳብ ተማርን፤ በዚህም ብዙ ለውጦችን አግኝተንበታል ስትል ገልጻለች።
እኔና እህቴ ወደዚህ ከመምጣታችን በፊት ተነጋግረን፣ ተመካክረንና ወስነን ነው የመጣነው ያለችው ስመኝ ፤ አሁን ላይ ስልጠናውን በብቃት አጠናቀን ለቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ በመሆናችን ደስተኛ ነን ብላለች።
የዘመናዊ መከላከያ ሰራዊት መርህን በመከተልና የሚሰጠንን ተልእኮ በላቀ ብቃት በመፈጸም ሀገራችንና ህዝባችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን ስትል ተናግራለች።
ሁለታችንም ብር ሸለቆ መሰልጠናችን እየተረዳዳን፣ እየተደጋገፍን፣ እየተመካከርን… ስልጠናውን በከፍተኛ ብቃት ለማጠናቀቅ አስችሎናል፤ ብቸኝነትን በማስወገድ ፈጥነን ተላምደን በሙሉ ልብ ስልጠናውን ለመከታተል አግዞናል ብላለች።
የስመኝ ታናሽ እህት የሆነችው መሰረታዊ ወታደር ቃልኪዳን ወርዶፋ በበኩሏ፤ የመከላከያ ሰራዊትን መቀላቀሌ ከልጅነቴ ጀምሮ በውስጤ የኖረውን ፍላጎትና ህልም እንዳሳካ አስችሎኛል ስትል ገልጻለች።
እኔና እህቴ ውስጣችን የነበረውን የሀገር ፍቅር የምንገልጽበት ተቋም ውስጥ በመግባታችን ደስታችን ወደር የለውም ያለችው ቃልኪዳን፤ ከራሳችን በፊት ቅድሚያ ለሃገርና ለሕዝብ የሚለውን የመከላከያ መርህ ለመተግበር ቆርጠን ተነስተናል ብላለች።
የሀገር ፍቅር ስሜታችን የመነጨው ከቤተሰብ ነው፤ የመሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደን መመረቃችን ትልማችንን እውን ለማድረግ እድል ይፈጥርልናል ብላለች።
“የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” እንደሚባለው ካሁን በኋላ ያገኘነውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመን የሚሰጠንን ተልእኮ በጀግንነት ለመወጣት ቁርጠኛ ነኝ ስትል አንስታለች ቃልኪዳን ።
የመከላከያ ሰራዊቱን ስቀላቀል ሀገሬን ለማገልገል ነው፤ የሃገሬንና የሕዝቤን ክብር ለማስጠበቅ እኔ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ ስትል ገልጻለች።
የዘመናዊ ወታደር ስብእናን በመላበስ በሀገራችን ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ፣ የተጀመረው ልማት ዳር እንዲደርስና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የድርሻዋን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግራለች።
ለዚህም በምትሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ የሚሰጣትን ተልእኮ ሁሉ በላቀ ተነሳሽነት በመፈጸምና ለተደማሪ ድል በመዘጋጀት ትልሟን በመተግበርና ዳር በማድረስ አሻራዋን ለማስቀመጥ እንደምትተጋም አረጋግጣለች።
የእነዚህን ብርቅዬ የሀገር ጀግኖች ታሪክ ለሕዝብ እንዲደርስ ለአብነት ተነሱ እንጂ ሶስት ወንድማማቾች ሆነው የገቡና ሌሎች ታሪኮች ያሏቸው ጀግኖች የመሰረታዊ ውትድርና ተመራቂዎች መኖራቸውን መመልከት ይቻላል።
ይህም ኢትዮጵያ የበርካታ ጀግኖች መፍለቂያ ሀገር መሆኗን የሚያሳይ እና ጀግንነት ደግሞ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በድምር ውጤት በሀገር የሚገለጥ ሲሆን፤ የእህትማማቾቹ ታሪክ ከቤተሰብ የተገኙ ጀግኖች ናቸው።
የጀግንነት ዋናው ምእራፍ ፍላጎት፣ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝትና ዝግጁነት በመሆኑ ሁለቱ ባለታሪኮቻችን እነዚህን ጉዳዮች አሟልተው በግንባር ለሚመዘገበው ድል አኩሪ ተጋድሎ ለመፈጸም የተዘጋጁ ናቸው።