''ቦር ተራራ'' የየሞች የፈውስ ምድር - ኢዜአ አማርኛ
''ቦር ተራራ'' የየሞች የፈውስ ምድር
(በእንዳልካቸው ደሳለኝ ከወልቂጤ ኢዜአ ቅርንጫፍ)
የም ዞን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ይገኛል። በዞኑ የቦር ተራራ ዋነኛው የመድኃኒት እጽዋት መገኛ እና ምንጭ በመሆኑ የሞች በየዓመቱ ጥቅምት ወርን ጠብቀው በ17ኛው ቀን ከዚህ ተራራ በህብር ሆነው የመድኃኒት እጽዋት ለቀማ ስነ-ስርዓት ያካሂዳሉ፤ ይሰባስባሉም ።
የቀደምት የየም አባቶችና እናቶችን በማሳተፍ የሚከወነው የመድኃኒት እጽዋት ለቀማ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 939 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው ቦር ተራራ ላይ ነው። በዚህ ተራራ ላይ በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን የሞች ለዓመት የሚያገለግላቸውን የመድኃኒት እጽዋት ይለቅማሉ። ተግባሩንም አዋቂዎች በጋራ ሰብሰብ ብለው ለመድኃኒት የሚውለውን ቅጠል በጥሰው፣ ስር ምሰው፣ አስሰውና መርጠው ይሰበስባሉ። ይህም የመድኃኒት እጽዋት ለቀማ ስርዓት "ሳሞ ኤታ" ተብሎ ይጠራል ።
አያምጣውና ህመም ሲከሰት ታማሚውን ሰው ወይም እንስሳን ከበሽታው ለመፈወስ የተዘጋጀው ባህላዊ መድሃኒት በባህላዊ ሃኪም ትዕዛዝ መሰረት በህመሙ ልክ ይታዘዝለታል። መድሃኒቱን ለመጠቀምም የጠቢባን አባቶችን ፈለግ ተከትሎ መፈፀም የግድ ይላል።
የሞች አጅግ አስገራሚ እና አስደናቂ የሆኑ የበርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤት ናቸው ካስባሏቸው እሴቶች መካከል ይህ ለየት ያለው ክዋኔያቸው አንዱ ነው፡፡ አባቶች ታዳጊና ወጣቶችን አስከትለው ወደ ቦር ተራራ በመውጣት የሚፈፅሙት ባህላዊ ክዋኔ በመሆኑም ከትውልድ ወደ ትውልድ ቅብብሎሹን ጠብቆ እስከ አሁን እንዲዘልቅ እድርገውታል።
በየሞች ዘንድ የባህላዊ መድኃኒት አዋቂዎች ከሚባሉት መካከል አንዱ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም፤ የመድኃኒት ዕፅዋት ለቀማ ልምድን የቀሰሙት ከአባታቸው መሆኑን በመግለፅ አያታቸው ከቅድመ አያቶቻቸው በመውረስ እዚህ እንዳደረሱት ይናገራሉ። የቦር ተራራ ለመድሃኒት ዕፅዋት ለቀማው የተመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዱም ቦታው ተራራ በመሆኑ ማንም ያልደረሰባቸው የተለያዩ እፅዋትን ለማግኘት አመቺ ከመሆኑ ጋር ያያይዙታል።
በሌላም በኩል ጠዋት ፀሐይ ስትወጣ መጀመሪያ የምታገኘው ተራራውን በመሆኑና ክረምቱ አልፎ ጥቅምት ሲገባ የተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎችን በብዛት እና በዓይነት ለማግኘት ተመራጭ ወቅት መሆኑም ቦታው የተመረጠበት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል። በጥቅምት 17 ለመድኃኒትነት የሚያገለግለው ዕፅዋት ቅጠልም በየፈርጁ ተለቅሞ እና ተቀምሞ ይቀመጣል ሲሉም አስረድተዋል። የተዘጋጀው ባህላዊ መድኃኒትም ለሰው ልጆችና ለቤት እንስሳት ያገለግላል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ይኸው በዚህ ቀን የተለቀመው የመድኃኒት ዕፅዋት ከዚህኛው ጥቅምት 17 እስከሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 17 ድረስ እንደሚያገለግልም አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡
የባህል መድኃኒት ሰብሳቢዎች እና ተጠቃሚዎች ጊዜውን ጠብቀው ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ቦር ተራራ እንደሚመጡ የሚገልጹት የባህል መድኃኒት አዋቂው ዛሬ ዛሬ እሳቸውን ጨምሮ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ የባህል መድኃኒቶችን በመሸጥ ኑሯቸውን እየመሩ የሚገኙ አያሌ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉም ይናገራሉ።
ሌላኛው የባህል መድኃኒት አዋቂው አቶ ወልደመስቀል ጆርጋ በበኩላቸው በየሞች ዘንድ የተዘጋጀው የመድኃኒት ዕፅዋት ጥቅም ላይ የሚውለው ህመም ሲያጋጥም ብቻ ሳይሆን በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል መሆኑን ጠቁመው መድኃኒቶቹም ብቻቸውን እንዲሁም ከምግብ ጋር በመመገብ ለጥቅም እንደሚውሉም አንስተዋል።
የየም ምድር የበርካታ የመድኃኒት ዕፅዋቶች መገኛ አካባቢ " የፈውስ ምድር " ነው የሚሉት ደግሞ በየም ባህላዊ መድኃኒት ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር እና ተመራማሪ ለማ ንጋቱ (ዶ/ር) ናቸው።
ከየሞች አያሌ የባህል ዕሴቶች መካከል የባህል መድኃኒት ለቀማና ቅመማ አንዱና ዋነኛው የሀገር በቀል እውቀት ማሳያ መሆኑን ገልፀው የመድኃኒት ዕፅዋት ለቀማ ስነ-ስርዓቱ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ዛሬ ላይ የደረሰ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ማህበረሰቡ የራሱንም ሆነ የእንስሳትን ጤና የመጠበቅ የቆየ ባህል ያለው መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው የባህላዊ መድኃኒት ለቀማው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚሳተፉበት ዓመታዊ ክዋኔ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ሌላው ገራሚው ነገር ይላሉ አጥኚው ታላላቆች ታናናሾቻቸውን አስከትለው የለቀማ ሂደቱን የሚያስረዱበት መንገድ ደግሞ ስርዓቱ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያስችል ትውልድ ተሻጋሪ የሀገር በቀል እውቀት ሽግግር ስርዓት ማሳያ እንደሆነም ነው የገለጹት። በዚህም ሂደት የሚነገሩ ስነ-ቃሎች መሞጋገስ፣ ጭፈራና ደስታ ይስተናገድባቸዋል። ይህም ማህበራዊ ትስስርን ይበልጥ የሚጠናክሩበትን ሁነት የሚፈጥር ስርዓት ነው።
የየም ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ሞጋ በበኩላቸው የቦር ተራራ የመጀመሪያውን የማለዳ የፀሐይ ጎህ የሚፈነጥቅበት የንጋት ብርሃን ቀድሞ የሚያገኝ በመሆኑ፥ በዚህ አካባቢ የሚገኙ እጽዋት በሽታን የመከላከልና ፈዋሽነታቸው ከፍተኛ ነው ተብሎ ስለሚታመን ለዚህ ክዋኔ ቦታው መመረጡን ነው የሚገልፁት። ለዚህም ነው የሞች ይህንን ስፍራ ከሌሎች ቦታዎች አስበልጠው የሚወዱት፤ በየዓመቱም ጥቅምት 17 ቀን ወደ እዚህ ስፍራ በማቅናት ለዓመት ፍጆታ የሚያገለግላቸውን መድኃኒትም ይሰበስቡበታል ብለዋል።
ጥቅምት 17 በየም ዘንድ ለየት የሚያደርገው ሌላው የመድሃኒት ዕፅዋት ለመልቀም እና ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን የለቀማውን ትዕይንት ለመመልከት የሚመጡ ቱሪስቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ሌላው ትልቁ ትሩፋት ነው ይላሉ። የመድኃኒት ዕፅዋት ለቀማው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት በመሆኑ፥ ለአብሮነት እና ሃገር በቀል እውቀት ለመቅሰም ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው አቶ መስፍን የገለፁት።