በትግራይ ክልል የመስቀል በዓል አከባበር - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የመስቀል በዓል አከባበር

የመስቀል በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በልዩ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
በዓሉ እንደየአካባቢው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
በትግራይ ክልልም የመስቀል በዓል እንደሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ በናፍቆት ከሚጠበቁና በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት ተርታ ይመደባል።
ለዚህም ሲባል የተለያዩ ዝግጅቶች ከበዓሉ ዋዜማ በፊት እንዲጠናቀቁ የሚደረግ ሲሆን፥ በተለይ በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ዘመድ አዝማድ ተጠራርተው የሚገናኙበት የፍቅርና የአብሮነት በዓል ሆኖ ይከበራል።
የክርስቶስ ግማደ መስቀል በንግስት ኢሌኒ አማካኝነት መገኘቱን በማሰብ በየዓመቱ መስከረም አጋማሽ ላይ የሚከበረው የመስቀል በዓል የመስቀል ኃያልነት፣ እውነት በተደበቀበት ለዘላለም እንደማይቀርና ፍቅርን አብዝቶ የሚሰበክበት ከዚህ ባለፈም እርቅ የሚወርድበትና ደስታ የሚገለጽበት አጋጣሚ መሆኑም ይገለጻል።
በትግራይ የበዓሉን ታላቅነትና ክብር ለማድመቅ ምእመናን ጽዱ ልብስ ለብሰውና የተለያዩ ዝማሬዎችን በማሰማት ደመራ ወደሚደመርበት ሥፍራ ችቦ ይዘው በመሄድ ደምራውን በማቀጣጠል የሚያከበሩት ሲሆን፣ በእለቱ የቤት እንስሳት ጭምር ቀንዳቸውና ጀርባቸው ላይ ቅቤ ተቀብተው እንዲያርፉ ይደረጋል።
ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤታሞች፣ አብሮ አደጎችና የበዓሉ ታዳሚ እንግዶችም ተሰባስበው ማለዳ ላይ ገንፎ በማዘጋጀት ይመገባሉ።
የእንስሳት እርድ በማከናወን ባህላዊ መጠጦችን በማዘጋጀት በዓሉን የፍቅር፣ የመሰባሰብ፣ የአንድነትና ተካፍሎ የመብላት በዓል መሆኑን በተግባር የሚያሳይበት ክስተት ሆኖ ያልፋል።
"ዓኾይ ዓኾኾይ" የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ በማለትም ችቦ ተሎኮሶ በየቤቱ በመዞር የምረቃ እና ለሚቀጥለው ዓመትም በሰላምና ደስታ እንዲሁም እድሜና ጤናን በመመኘት ይከወናል።
የአደባባይ በዓል የሆነው የመስቀል በዓል በዝማሬ፣ በሆታና እልልታ የሚገለጽ ሲሆን፤ ወርሃ መስከረም እሸት አሽቶ አበቦች አብበውና ምድር ልዩ ልምላሜን ተላብሶ የሚታይ በመሆኑ ልክ በታሪኩ እንደሰፈረው የሰላም፣ የእውነትና የአንድነት በዓል መሆኑን በተግባር የሚታይበት ነው።