ባሕር በር -የታሪክና የእድገት ስብራት ወጌሻ - ኢዜአ አማርኛ
ባሕር በር -የታሪክና የእድገት ስብራት ወጌሻ
ባሕር በር የታሪክ እና የእድገት ስብራት ወጌሻ
በቀደሰ ተክሌ
የምሥራቅ አፍሪካዋ ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስሟ ገኖ እንዲነሳ ካደረጓት መካከል የሰው ዘር መገኛነት፣ የራሷ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ቋንቋና ፊደል ያላት ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ ተጠቃሽ ነው ። የገናና የጥበብ ባለቤት መሆኗን አክሱም እና ላሊበላ ዛሬም ቆመው ይመሰክሩላታል።
በጥንት ጊዜ ወደብ የስልጣኔ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መገለጫ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያም ስሟ ጎልቶ ይነሳ ነበር። ወደብ ዓለምን እርስ በእርስ ከማስተሳሰር ባለፈ የግብይት የጀርባ አጥንት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፤ ዛሬም እያገለገለ ይገኛል። ሀገራት አዋጭ የንግድ ስትራቴጂ ቀይሰው የተለያዩ ወደቦችን የመጠቀም ልምዳቸው በታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚነሳ ነው። የንግድ ሥርዓታቸውን በወደብና በየብስ ከሚያከናውኑ የዓለም ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመነ መንግስታት የተለያዩ ወደቦችን በባለቤትነት አስተዳድራለች። ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ደርግ መንግስት ድረስ አዱሊስ፣ አሰብ፣ ዘይላ፣ ምጽዋና ሌሎች ወደቦችን ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ትገለገል ነበር።
ይሕ የኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት ታሪክ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የዘለቀ እንደነበር በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሰቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምሕርት ክፍል መምሕር አጥናፉ ምትኩ ይናገራሉ። ወደብ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነም አውስተዋል።
በታሪክ ኩነት ውስጥ የተፈጠረ ሴራና ተንኮል ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። ይሕም ከሆነ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። በዚሕም ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ብር እየከፈለች የወጪ እና ገቢ ንግድን የማንቀሳቀስ እዳ ተጭኖባታል።
ይሕም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። የወደብ አገልግሎት ነጻነት ማጣት፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ መጨመር፣ ማዳበሪያን ጨምሮ አስፈላጊ ግብአቶች መዘግየትና በወቅቱ አለመድረስ፣ በዚሕም የሰብል ልማት ስራዎች ላይ ችግሮች መስተዋል ከባሕር በር ባለቤትነት እጦት ጋር የመያያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። እነዚሕ ችግሮች ደግሞ ተደማምረው ለኑሮ ውድነት መፈጠር አስተዋጾኦ ይኖራቸዋል ማለት ይቻላል።
በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረው ስብራት እያስከተለ ያለው ጉዳት አሁን ላይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ በታሪካዊ ዳራ መሠረት መጠገን ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ከ130 ሚሊዮን ያሻቀበ የሕዝብ ቁጥር፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሀገራዊ የቆዳ ስፋት ገፊ ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል ከዚሕ ቀደም የነበረው የሀገሪቱ ባሕር በር ባለቤትነት ማስረጃ ዛሬ ላይ አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
መንግሥት የጀመረው የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጥያቄ በመሬት ተዘግቶ የመኖር ታሪክ እንዲያበቃ የሚያደርግና በዓለም አቀፍ ሕግ ተፈጥሮን በጋራ ተጠቅሞ የመልማት መብትን የሚያስጠብቅ መሆኑ እውን ነው። ለሦስት አስርት ዓመታት ታፍኖ የቆየው የቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ የመንግስት ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ ዜጎችም አጥብቀው በመያዝ መልስ እስኪያገኝ ድረስ መስራት ይጠበቃል። የሀገርና የሕዝብ የዘመናት ጥያቄ የሆነው የባሕር በር እስኪሳካ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅ መምሕር አጥናፉ ይገልጻሉ።
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን የታሪኳና ዕድገቷ ወጌሻ ነው ያሉት መምሕር አጥናፉ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለመጠቀም የሚያስችላት ታሪካዊ መብት አላት። ይሕን ታሪካዊ መብቷን የምታረጋግጥበት ትልቁ መሣሪያ ደግሞ ያላት ጠንካራ የዲፕሎማቲክ አቅሟ ነው። ከዓለም ሀገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ተናግሮ ለማሳመን እውነታን ለመግለጽ የሚያስችላት ነው። ይሕንንም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓለም ፊት አረጋግጣለች። ይሕን የሕዳሴ ድል በቀይ ባሕር ላይ የማትደግምበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
በተለይ ኢትዮጵያ ያላት የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ በዓለም ላይ ተቀባይነት ያለውን ሀሳብ ይዛ እንድትቀርብ እያስቻላት ይገኛል። ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጠው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ተፈጥሮን ተባብሮ በማልማት እንጠቀም የሚል መሠረት ያለው ነው።
መምሕር ይስሐቅ ንጉሤ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሰቲ የምጣኔ ሀብት መምሕር ሲሆኑ የባሕር በር ጉዳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማጠንጠኛ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ በፈጣን ዕድገቷ ላይ መሰናክል ሆኖ መዝለቁን ተናግረዋል።
በተለይ የዓለም ሀገራት ከፍተኛው የንግድ፣ የኢኮኖሚና ሀብት እንቅስቃሴ የሚታይበት እና የሀገራት የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት የቀይ ባሕር ቀጠና ላይ ያለውን አብሮ የመስራትና ከማደግ ዕድል ኢትዮጵያ ያለአግባብ መገለሏን ያነሳሉ።ይሕም በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና በሌሎች ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያገለጹት።
የባሕር በር ጥያቄ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማሳለጥ ሀገሪቱ ከልመና ለመውጣት ያላትን ዕድል እንድትወስን ያስችላታል የሚሉት መምሕሩ ፤ለስኬቱም የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም ነው የገለጹት።
እንደ መምሕሩ ገለጻ ከዓለም አቀፍ መርሆችና ስምምነቶች እንዲሁም ካለን መልከአ ምድራዊ አቀማመጥና ታሪክ አንጻር ለኢትዮጵያ የባሕር በር ተገቢ ነው። ይሕ እንዲሳካም መንግስት ካሳየው ቁርጠኝነት በተጨማሪ ሁሉም በተቀናጀ መንገድ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርበታል። መንግስት የዘመናት የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የባሕር በር ጉዳይ በግልጽና በይፋ መረጃ በመስጠት ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆንም ጭምር እያደረገ ያለውን ጥረትንም አድንቀዋል።
ታሪክ በኩነቶች መካከል መጥፎም መልካም ሆኖ ያልፋል። በታሪክ የባሕር በር ባለቤትነታችን የገጠመውን ስብራት ለመጠገን የሚያስችል ወጌሻ ያስፈልጋል። በታሪክ ሂደት መልካሙ ወደ መጥፎ ሁኔታ እንደሚቀየር ሁሉ የተበላሸን ወደ መልካም የመቀየር ዕጣ ፈንታ ያለው የዛሬው ትውልድ ላይ ነው። ለእዚሕ ደግሞ ትውልዱ በሕዳሴው ግድብ ከመንግስት ጎን ሆኖ ያሳየውን አንድነትና ሕብረት በባሕር በርም መድገም አለበት። ታሪካዊ ዳራን፣ ዲፕሎማሲን፣ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታና ሕግን ተከትሎ በአብሮነት ከተሰራ ያኔ የተበላሸው ይቃናል፤ ያጣነውን እናገኛለን።
"እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" ዓይነት እንስሳዊ ግብር በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሊሰማ አይገባም፤ መሰማትም አይኖርበትም። ኢትዮጵያ ብታደግ ለቀጣናው ኩራት፤ ለአፍሪካም ልዕልና እንጂ ጥፋት የሚያስከትል እንዳልሆነ መገንዘብና የትብብር ልማትና ዕድገትን ባሕል ማድረግ ሊለመድ ይገባል። ሰላም!