የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አብዮት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አብዮት

በሙሴ መለስ/ኢዜአ
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ኃይል ዋንኛ ማዕከል በመሆን ላይ ትገኛለች።
የተፈጥሮ ውበቷን ከኢኖቬሽን ጋር በማስተሳሰር የአየር ንብረትን የማይበክሉ የተለያዩ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን እየተጠቀመች ይገኛል።
አዲስ አበባ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን እየተጠባበቀች ነው።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ስራ በጉባኤው ከምታቀርባቸው ተሞክሮዎች መካከል ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ ከእንፋሎት ሃይል፣ ባዮማስ ከእንስሳትና እጽዋቶች ተረፈ-ምርት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት። ይህም የሚያሳየው አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች መሆኑን ነው።
ኢትዮጵያ ከጂኦተርማል 10 ሺህ ሜጋ ዋት ከንፋስ ኃይል ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት እምቅ አቅም አላት።
ግንባታው የተጠናቀቀው እና 5 ሺህ 200 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ከብክለት ነጻ የኃይል ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
መንግስት የሀገሪቱን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ በዋና ዋናዎቹ የወንዞች ተፋሰሶች የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን በማልማት ላይ ይገኛል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅዷ ኢትዮጵያ የምታመነጨውን የኃይል መጠን አሁን ካለበት 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ ግብ ተቀምጧል። የተሻሻለው የኢነርጂ ፖሊሲዋም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ዕውነታ መሰረት ያደረገ እና ጎረቤት ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
ይህንንም እውን ለማድረግ በመንግስት ከሚለሙት የኃይል ምንጮች በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ ኃይል ተመርቶ የኃይል አቅርቦቱ እንዲሻሻልና ዘላቂ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በ2009 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክት በአዋጅ ቁጥር 1076/2018 ተመስርቷል።
በዚህ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ስምንት የፀሐይ ኃይል፣ አምስት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ እና አምስት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶችን ለማልማት እየተሰራ ይገኛል።
ከስምንቱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እስከ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።
ጋድ 1 እና 2፣ ዲቼቶ፣ ወራንሶ፣ ሁመራ፣ ወለንጪቲ፣ መቀሌ፣ ሁርሶ እና መተማ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹ ናቸው።
አዳማ አንድ፣ አዳማ ሁለት፣ አይሻ ሁለት እና አሸጎዳ ከንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
የእንፋሎት (ጂኦተርማል) ኃይልን በተመለከተም በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክት ኮርቤቲ ከሚባል የግል አልሚ ጋር መንግስት ተዋውሎ ድርጅቱ የሚያመርተውን 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል።
በአጠቃላይ በተለያዩ የኢነርጂ አማራጮች የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ሽፋንን 54 በመቶ ማድረስ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም አማካኝነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 65 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብሔራዊ የኃይል ቋት እንዲሁም ቀሪው 35 በመቶ ከኃይል ቋት ውጭ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ የማድረግ እቅድ ተይዟል።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እያቀረበች ያለው አረንጓዴ የኃይል አማራጭ የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል እና ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የተሻሻለው የኢነርጂ ፖሊሲዋም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ዕውነታ መሰረት ያደረገ እና ጎረቤት ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
በርግጥ ከሕዳሴው ግድብ ባሻገር ሌላው ከአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የኮይሻ ኃይል ማመንጫም ለቀጣናዊ ትስስር መፋጠን ሌላው እድል ነው።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገራት ኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ ነው። በተጨማሪም በቀጣናው ዘላቂ የኤሌክትሪክ ገበያ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ክፍለ አሕጉራዊ ጥረት ነው።
ጥረቱ የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ቋት (The Eastern Africa Power Pool-EAPP) በቀጣናው ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የሃይል ንግድ እና የሃይል መስመር ትስስርን ለማሳለጥ እኤአ በ2005 የተቋቋመ ተቋም ግብ እውን ከማድረግ ባለፈ አሕጉራዊ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን ያፋጥናል።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኢነርጂ አብዮት የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ስራ እና የደን ልማትን የሚያግዝ ነው።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እየተቃረበ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኃይል አሻራውን ለአፍሪካ ለማሳየት ተዘጋጅታለች።
አረንጓዴ የኃይል አማራጮች ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ መገንቢያ ዋና ምሰሶዎች መካከል ይጠቀሳል።